top of page

Tribute by Tsehay Demeke

ታላቁ ኢትዮጵያዊ ምሁር - ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ተማሪ ሳለሁ ደርግ ስልጣን ከመያዙ በፊት እሰማ ነበር። ዝነኛ ነበሩ። ኮሌጅ ስገባ የሳቸው ተማሪ ብሆን የሚል ምኞት ነበረኝ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን በቅርብ ያወቅኋቸው አሜሪካ ጥቂት አመታት ከኖርኩ በኋላ ነው። ካወቅኋቸው ከ30 አመት በላይ ሆኗል።


ኢ. ኢ. ዲ. ኤን (EEDN – Ethiopian Email Distribution Network) በመባል ላቋቋምነው የ ኢ-ሜል መሰባሰቢያ መድረክ ከተሳታፊዎቹ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ነበሩ። በስብስቡ ውስጥ የተለያዩ አገር-ነክ ውይይቶች ይካሄዳሉ። ጥሩ ጥሩ ሃሳቦች ይፈልቃሉ። የዕርዳታ ገንዘብ ይሰበሰባል። ሃሳቦች ሲፋለሱ መስማማት ሲቸግር እሰጥ-አገባው አንዳንዴም ከረር ይላል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ነገሮችም ተፈጽመዋል። የኢትዮጵያ አገራዊ ጉባዔ ተፀንሦ የተወለደውም እዚሁ ኢ. ኢ. ዲ. ኤን ውስጥ ነበር። ሃሳቡን በመግፋት እውን እንዲሆን ከደከሙት ውስጥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ተቀዳሚ ናቸው። የኢትዮጵያ አገራዊ ጉባኤ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማሰባሰብ ተቀዳሚና ወደ ፊት ለመጡ እንደ ቅንጅት ላሉ ድርጅቶች መዋቅር ፈር-ቀዳጅ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። የፕሮፌሰር ጌታቸው ሚና ትልቅ ግምት ሊሰጠው ይገባል።


በፕሮፌሰር ጌታቸው ታላላቅ እና ማንኛውም ስራቸው፤ የባለቤታቸው የወ/ሮ ምስራቅ አማረ እጅ እንዳለ ሁል ጊዜ ፕሮፌሰር ያነሳሉ። ሁላችንም ለዚህ የዓይን ምስክር ነን። በስብሰባዎች በሰላማዊ ሰልፎች በማንኛውም የኢትዮጵያ ጉዳይ ወ/ሮ ምስራቅ ያልተገኙበት ቦታ የለም። በዚህ አጋጣሚ ወ/ሮ ምስራቅን ከባለቤታቸው ጎን ሆነው ላደረጉት መስዋዕትነት እና ለኢትዮጵያ ላደረጉት የጋራ አስተዋፆ የልብ ምስጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ።


ፕሮፌሰር ጌታቸው፤ ደከመኝ ሳይሉ ለኢትዮጵያ ላደረጉት አስተዋፅዖ ገለጻ ለማቅረብ፤ የለገሱትን የዕውቀት ችሮታ ለመዳሰስ፤ ዕውቀቱም ሆነ ብቃቱ ስለሌለኝ ለታሪክ ፀሃፊዎች እተወዋለሁ። ለኔ ፕሮፌሰር ጌታቸው፤ መሪዬ፤ አስተማሪዬ፤ መካሪዬ እና አባቴም ነበሩ።


የአገሬን ፍቅር የምወጣው ከፕሮፌሰር ጌታቸው በማገኘው ትምህርት ነበር። በአገሬ ጉዳይ ለመሳተፍ ይረዳኝ ዘንድ ፕሮፌሰር ምን አሉ ብዬ ማድመጥ በቂዬ ነበር። በኢትዮጵያ አገራዊ ጉባዔ፤ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፤ በክተት፤ በኢትዮጵያዊነት፤ በኢትዮጵያችን ድርጅት ከፕሮፌሰር ጌታቸው ጋር አብሬ አገልግያለሁ።


ፕሮፌሰር ጌታቸው ሰው አክባሪ፤ ትሁት፤ ርቱዕ አንደበት ያላቸውና በአገር ጉዳይ ፅኑ አቋም ያላቸው ከእግዚአብሄር ለኢትዮጵያ የተሰጡ አስተማሪና መሪ ነበሩ። ስራቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ህያው ሆኖ ይኖራል።


ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ቀልድና ጨዋታ የማይለያቸው፤ በበለጸገው የቋንቋ ችሎታቸው በአጭሩ ሃሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ፤ የብዙ ቋንቋ ባለቤት ናቸው።


አብሬያቸው ካሳለፍኩት አመታት ከሰማሁት፤ ከገጠመኝ የሚያዝናኑ እና ትምህርት የሚሰጡ አባባሎች ጥቁቱን ላካፍላችሁ።

• ፕሮፌሰር ጌታቸው ስማቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲጽፉ ሆሄያቱን (ስፔሊንጉ) በቅጡ ካልተጻፈ አይቀበሉም። (GETATCHEW but not GETACHEW) የፕሮፌሰርን ስም ያካተተ ደብዳቤ ጽፌ ላኩላቸው። ለላክሁት ደብዳቤ መልስ አልሰጡኝም ብዬ ብላቸው፤ የጻፍከው ለኔ አልመሰለኝም ለዚህ ይሆናል ያላነበብኩት ብለው ሳቅ አሉ። ለርስዎማ ነው ብዬ ብል፤ እስቲ በቅጡ ተመልከተው ብለውኛል። ከዚያ ቀን ወዲህ አስተካክዬ መጻፍ ጀመርኩ።

• ፕሮፌሰር ጌታቸው ስብሰባ ሲጠራ በሰዓቱ እንዲያውም ቀደም ብለው በመገኘት የታወቁ ናቸው። አርፍደው የሚመጡ ሰዎች አይታጡም። አንዳንዱም ስብሰባው ሊያልቅ ሲል ብቅ ይላል። በአንድ የቴለኮንፍራንስ ስብሰባ ላይ አንዱ እድምተኛ በጣም አርፍዶ ከመጣ በኋላ፤ ለተሰብሳቢው ስለማርፈዱ ይቅርታ ጠየቀ። ፕሮፌሰር ጌታቸውም ሲመልሱለት፤ አይ ግድ የለም ከስብሰባው ሳንወጣ ደርሰኽብናል ብለው ሲሉ፤ ታዳሚውን በሞላ በሳቅ አዝናንተውታል።

• መኢአድ ሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ማኅበር ውስጥ አንድ ዕለት በአገር ጉዳይ የከረረ ስብሰባ ስናካሂድ፤ (Let us argue) የሚለውን ቃል አንዱ ባልደረባችን ተርጉሞ፤ እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ እንጨቃጨቅ አለ። ስብሰባው እንደተበተነ እንጨቃጨቅ የሚለው ቃል ገርሞኝ፤ ሁለተኛ ደረጃ (high school) ተማሪ ሳለሁ፤ የአማርኛ አስተማሪዬ እንዳስተማሩኝ መጨቅጨቅ የሚለውን አርዕስት ለማርባት ሞከርኩ --- መጨቅጨቅ = አርዕስት፤ ጨቅጫቃ = የግብር ቅፅል፤ አጨቃጨቅ = ሳቢ-ዘር፤ ጨቅጭቆ = ቦዝ አንቀፅ.... እያልክ ከጻፍኩ በኋላ ፕሮፌሰር ጌታቸውጋ ስልክ ደውዬ እርባታውን ካነበብኩላቸው በኋላ በትክክል አርብቼው እንደሆነ እንዲነግሩኝ ጠየቅኋቸው። ጊዜ ሳይፈጁ ከመቅጽበት - ፀሐይ፤ ጭቅጭቅ አይረባም አሉኝ። ሲከነክነኝ አድሬ በነጋታው የቱ ላይ ነው የተሳሳትኩት? አልኩዋቸው። ሳቅ ብለው ነገርኩህ እኮ በሰላም መስራቱ አይሻልም? ጭቅጭቅ እኮ አይረባም አሉኝ። የኔ ነገር የፕሮፌሰር ጌታቸው የጠለቀ አመለካከት አልገባኝ ኑር እንጂ፤ መልሳቸው የስዋስው እርባታ ሳይሆን በሰላም ተወያዩ ማለታቸው ነው።


ከፕሮፌሰር ጌታቸው ጋር አብሬ ያሳለፍኳቸው ደቂቃት ሁሉ የዕውቀቴ ማዳበሪያ ነበሩ።

ነብሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልን። ባለቤታቸውንና መላው ቤተሰባቸውን መጽናናት ይስጥልን።

9 views0 comments

コメント


bottom of page