top of page

Tribute by Tariqu Hailu and Shoaye Legesse

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሲታወሱ በባህል ታሪክና ሥነጽሑፍ ችሎታቸውና ተመራማሪነታቸው በሃገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ታዋቂነትን ያተረፉ ታላቅ ሰው ነበሩ ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ:: ለብዙ ጊዜ በሕመም ቆይተው እንደጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ሰኔ 10 ቀን 2021 ከዚህ ዓለም ዕረፍታቸው ሆነ:: 90 ዓመታቸው ነበር:: ብዙዎች «የዕውቀት ሁሉ ማህደር» «ተንቀሳቃሽ ቤተመፃሕፍት» ብለው የሚጠሯቸው የእኚህ ታላቅ ሰው ዕልፈት ዕውቀት ተጠቅልሎ ወደመቃብር እንደወረደ የሚቆጠር ነው ይላሉ ኘሮፌሰር አዱኛው ወርቁ የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ተመራማሪ። «በገና ደርዳሪዎች እንዲህ ትልቅ ሲሞት እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር ፆመ ድጓ ይዞ ገባልህ መምህር ይላሉ:: ብዙ ዕውቀትን ነው ተሸክመው የሄዱት የማይተኩ ሰው ናቸው:: የእሳቸውን ፈለግ መከተል ነው እንጂ እርሳቸው ከሚገባው በላይ ግዴታቸውን ተወጥተው አልፈዋል::» ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነበሩ:: ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ ያበረከቱት አስተዋፅዎ የጎላ ነው:: ጥንታዊ የኢትዮጵያ መዛግብት ጥናት ላይ እስከዘመናቸው ፍፃሜ ድረስ ገፍተውበት ከፍ ያለ እውቅና አግኝተውበታል:: የታሪክ ምሑሩ ዶክተር አሉላ ዋሴ ከቤተሰብ ጌታቸው ኃይሌ ጋር ቤተሰባዊ ቅርርብ አላቸው:: ኘሮፌሰር ጌታቸውን «የባህልና የታሪክ ጠንካራ ዋልታ» «አስተዋይ እና ጥልቅ ዕውቀታቸውንም ለሌሎች ማካፈል የቻሉ ነበሩ» ሲሉ ይገልጿቸዋል:: ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በቀድሞው ሸዋ ክፍለሃገር በሸንኮራ ወረዳ ከአባታቸው ከግራዝማች ኃይሌ ወልደየስና ከእናታቸው ወይዘሮ አሰገደች ወልደ ዩሐንስ እንደጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ታኅሣስ 19 ቀን 1931 ነበር የተወለዱት። ከቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ የመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎች አንዱ ሲሆኑ በግብፅ በጀርመን በእስራኤልና በአሜሪካን ሀገር የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከፍተኛ እውቅና ያስገኘላቸው ጥንታዊ የኢትዮጵያ መዛግብት ጥበቃ ይደረግላቸው ዘንድ ማይክሮ ፊልም በሚባለው ቅጂ መጠበቂያ አንዲመዘገብ ያደረጉት ጥረት ነው። በሜኒሶታ ቅዱስ ዩሐንስ ዩኒቨርሲቲ በማይክሮ ፊልም ተቀርፀው የሚገኙ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚመለከቱ ጥንታዊ የግዕዝ ሥራዎችን ወደአማርኛ ተርጉመዋል። ከእነዚህም መካከል ደቂቀ አስጢፋኖስ፣ የአባ ባህርይ ድርሰቶች፣ ባሕረ ሃሳብ፣ ስለግዕዝ ሥነፅሑፍ የተዘጋጁ አንዳንድ ማስታወሻዎች እና ሌሎች ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ። ኘሮፌሰር ጌታቸው በእነዚህ ሥራዎቻቸው በርካታ ሽልማቶችን የተቀበሉ ሲሆን ከአፍሪካ የማርካርተር ሽልማትን ያገኙ ብቸኛው ሰው ናቸው። ከአሜሪካ መንግሥት በ1987 የተበረከተላቸው የማርካርተር የበሳል አዕምሮና ምጡቅ ተመራማሪ ሽልማት በመስኩ የመጀመሪያው ተሸላሚ አድርጓቸው የ340 ሺህ ዶላር አስገኝቶላቸዋል። በወቅቱ በዚህ በአሜሪካ ላንዳፍታ የተሰኘ መፅሔት ያዘጋጅ የነበረው አቶ መኮንን ገሠሠ ሜኒሶታ በመሄድ ቃለምልልስ አድርጎላቸው ነበር። አቶ መኮንን ኘሮፌሰርን በቅርበት ከሚያውቋቸው ግለሰቦች አንዱ ነው። «የማካርተር ፋውንዴሽን ግራንት ያሸነፉት ስለኢትዮጵያ የቆዩ መጽሐፍት ላይ የሚያደርጉት ጥናት እየተረጎሙ በመመዝገብ ከሚያደርጉት ጥናት አንፃር ላደረጉት አስተዋፅኦ የ340 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር ያገኙት። በ1987 ለንደን በሚገኘው የብሪታንያ አካዳሚ አባል እንዲሆኑ ተጋብዘው ሄደው ለአባላት የሚሰጠውን ማዕረግ ፌሎው ኦቭ ዘብሪቲሽ አካዳሚ የሚባለውን አግኝተዋል። አካዳሚው በ83 ዓመት ዕድሜው ውስጥ ከዓለም ሊቃውንት መካከል ዝና ያተረፉትን እየመረጠ ነበረ ለአባልነት ይጋብዝ የነበረው። ከዶክተር ጌታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ማንኛውም አፍሪካዊ ተጋብዞ አያውቅም። ይኽ ነው አንዱ በውጭ የሚታወቁበት። በ1981 በሱዳን የነበሩና በኋላም አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያውያን ከወቅቱ የአሜሪካ ኘሬዚዳንት ቡሽና ምክትላቸውን አግኝተው በአቤቱታ መልክ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ አባት ናቸው።» ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አዘውትረው በየመገናኛ ብዙኃኑ እየቀረቡ ምሑራዊ ሐሳቦችን ሳይሰስቱና ሳይሰለቹ በማቅረብ ዕውቀትን ሲዘሩ ኖረዋል። የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ሥራአስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ወንድሙም በማተሚያ ድርጅታቸው ስለተሰየመው «ፍኖተ ጌታቸው ኃይሌ» ነግሮናል። ዶይቸ ቬለ በታላቁ ምሑር ጌታቸው ኃይሌ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል። ነፍስ ይማር!!! ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባው ያድምጡ

8 views0 comments

Comentarios


bottom of page