top of page

Fitihat Remembrance Remarks by Lij Nebyat Demessie



ጥቂት ስለ ዉድ አጎቴና አንጋፉዉ ምሁር ጋሼ ጌታቸዉ ሀይሌ

የተከበራችሁ የቅርብ ቤተሰቦች፣ የጋሼ ጌታቸው ጓደኞችና ወዳጆች፣ ክቡራትና ክቡራን ሁሉ፤ ጋሼ ጌታቸውን የሚያህል ትልቅ ሰው በማጣታችን፣ ሁላችንም ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል። ጋሼ ጌታቸው ለኢትዮጵያ ሕይወቱን ሙሉ ስውቶ የኖረ፤ አኩሪ ታሪክና ቅርሶቻችን በዕውቀትና ጥበቡ ያኖረ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል፣ ለእውነት፣ ፍትህና ራዐትህ የቆመ ነበር። ዛሬ አድባራችን፣ መከታችንን፤ ጋሼ ጌታቸውን አጥተናል። ነገር ግን፣ የማይደበዝዝ አሻራውን ጥሎልን ስላለፈ፤ ስሙና ታሪኩም ሕያው ሆነው ስለሚኖሩ በሱ ልንጽናና ይገባናል።

ጋሼ ጌታቸው ከልጅነቱ ጀምሮ የተለያዩ ችግርና ተግዳሮቶች በሕይወቱ አጋጥመውታል። በኢጣልያን ወረራ ጊዜ፣ ባንዳዎች፤ ጋሼ ጌታቸው ተወልዶ ያደገበትን ሸንኮራን አቃጥለውት ስለነበረና በዚያም ወቅት አባቱም ግራዝማች ሃይሌ ታመው ስለነበረ፣ ይፈወሱ ዘንድ፣ ለጸበል ወደ ኅመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት ቢሄዱም፣ ኢጣልያኖችና ባንዳዎች ባደረሱት ውድመትና ጥፋት ከአባቱ ጋር ሆኖ ተወልዶ ከአደገበት ቀዬ ተፈናቅሎ አንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ሆኖም ግን፣ ችግር፣ ግፍና መከራ ላፍታም ቢሆን ጋሼ ጌታቸውን አሸንፈውት አያውቁም። ይህ የሸንኮራው ጀግና፣ ችግርንና መከራን እራሱን አበሳውን ያሳየው አንደሆን ነው አንጂ፣ ለማንም ለምንም፣ ዋጋ ቢያስከፍለውም አንኳ፣ አጁን የሚሰጥ አልነበረም።

ጋሼ ጌታቸው በተማረበትና በሰራበት የሙያ ዘርፍ ሁሉ አንኳን የሚገዳደረው የሚወዳደረው አልነበረም። አብዛኛው ጊዜ በግዕዝ የተጻፉትን ጥንታዊ መጽሃፍትና መረጃዎች ካለሱ በስተቀር ሊመረምራቸው የሚችልም፣ የሚደፍርም አልነበረም። የሙያ ባልደረባዎቹም ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ሲያጡ አስቲ ፕሮፌሰር ጌታቸውን እንጠይቅ፣ አሱ ሊመልሳቸው ካልቻለ ማንም ሊመልሳቸው አይችልም እያሉ ባልደረባዎቹም ጭምር አድናቂዎቹ አንደነበሩ ይመሰክራሉ። St. John’s University በነበረበትም ጊዜ ኢትዮጵያን በሚመለከት ከ 100 በላይ ምሁራዊ ጥናቶች አሳትሟል አንዲሁም ደሞ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መጽሃፍትና ምስሎችን ድጅታይዝ በማድረግ እየጠፋ ያለውን የእትዮጵያን ታሪክ ከትውልድ ትውልድ ሊጠፋ በማይችል መልኩ እንዲተላለፍ ወደር የማይገኝለት ምሁራዊ፣ አገራዊም አስተዋጾዖ አበርክቷል።

ለነበረውም የላቀ እውቀትና አስተዋጾዖ የMacarthur Genius ሽልማት የመጀመርያው አፍሪካዊ ተሽላሚ አንደነበረም አይዘነጋም። ሌሎችም በርካታ ሽልማቶችም ተበርክቶለታል። በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንበብና መጻፍ የሚያውቅ ጋሼ ጌታቸውን ያውቃል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜም ዩኒቨርሲቲ ከማስተማርና ከመመራመር ባሻገር፣ መሃይምነት ከኢትዮጵያ አንዲጠፋ፣ የፊደል ሰራዊት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሆኖ ዘመቻውን በመምራት ኢትዮጵያዊያን አንዲበለጽጉ ከፍተኛ አስተዋጾዖ አበርክቷል። በወሎ ጠቅላይ ግዛት ተከስቶ የነበረውን ርሃብ በሚመለከት የመጀመርያውን ሪፖርት ከጻፉት ጋሼ ጌታቸው ዋነኛውና አንዱ ነበር። በደርግ ዘመንም በፓርላማ ተመርጦ ሸዋን በመወከል፣ ዴሞክራሲ የሚመሰረትበትንና ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት አንዲዘረጋ ከፍተኛ ንቃት አንዲፈጠር በማድረግ አገርና ሕዝቡን አገልግሏል።

ጋሼ ጌታቸው በ1996 ዓ.ም. የSociety of Ethiopians Established in Diaspora (SEED) ወይም ማህበራዊ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ ተሸላሚ ነበር፤ አንደውም diaspora የሚለውን ቃል ትርጉም ግዩራን ነው በማለት በትክክል ያሳወቀን ጋሼ ጌታቸው ነበር። በ2008 የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማትም አግኝቷል። ከBrtish Academyና ከሌሎችም አገር በቀልና ዓለም አቀፋዊ ድርጅትና ተቋሞች ሽልማቶች አግኝቷል። ሰዓት ስለሚገድበን ሁሉን ለመዘርዘር አይቻልም።

በበተሰብ ደረጃ ጋሼ ጌታቸው በጣም ትሁት፣ አክባሪና መካሪም ነበር። ከእውቀቱ ለማካፈልና ለማስተማር ሁሌም ፍቃደኛ ነበር። በርካታ ሰዎችም እውቀቱንና ምክሩን ለመቅሰም አንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለውን ምልከታ ለመስማት ቤቱ ድረስ ይመጡ አንደነበር አውቃለሁ። የራሴንም ጓደኞች ከአትዬ ምስራቅ ጋር ሆኖ በተለያየ ጊዜ አስተጋግደውልኛል።

በግሌ ጋሼ ጌታቸው በጣም የምወደው አጎቴ ነበር። በልጅነቴ ቅድመ አያቴ የሺመቤት ዲና ብዙ ጊዜ አብዬ ሃይሌ አያለች የቅርብ ዘመዷን የጋሼ ጌታቸውን አባት ስም በናፍቆት ትጠራው አንደነበር አስታውሳለሁ። አኔም አድጌ ከዝምድናችን ባሻገር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከጋሼ ጌታቸው ጋር ጥብቅ ግንጉኘት ለመመስረት በመቻሌ አግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።

አንድ ጊዜ በውጭ ያለነው እትዮጵያዊያን አንዴት ነው መደራጀት ያለብን ቢዬ ስጠይቀው፣ መደራጀት የሚፈልግ አለ? ብሎ በሸዋ አማርኛ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰው። ጋሼ ጌታቸው ከንግግሩ ብቻ አልነበረም ከጥያቄዎቹና ከዝምታውም ጭምር ብዙ ተምርያለሁ፣ብዙም ተምረናል።

ጋሼ ጌታቸው ምን ጊዜም ከመቃብሩ በላይ ስሙና ታሪኩ ሕያው ሆነው ይኖራሉ። የኛስ? እስካሁን ድረስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ፍለጋ ላይ ነኝ። በሕይወት እያለ መልሱን ለጋሼ ጌታቸው ለመንገር ባለመቻሌ በጣም ያሳዝነኛል። በጣምም ይቆጨኛል፤ ሆኖም ግን አኛ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ አንቆርጥም።

ጋሼ ጌታቸውን የምንወደውና የምናከብረው ከሆነ ስራዎቹ ለአገርና ለትውልድ አንዲተርፉ በእሱ ስም፣ መንፈስና ወኔ አገራችንን ከጥፋት ለማዳንና ለመታደግ መደራጀት ይኖርብናል። ለኛ ወጣቶች ጋሼ ጌታቸው የአገራችንን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት አንድንጠብቅ አስተምሮናል። በስራዎቹም አሳይቶናል። ከታሪኩም ጀግንነትን፣ ብርታትንና ጽናትን ተምረናል። ቀሪው ከኛ ነው!

በተረፈ ለማከብርህና ለምወድህ አጎቴ፣ ዳግም ላንገናኝ የመጨረሻው አረፍትህን አርፈሃል። አግዚአብሄር ነፍሥህን ለገነት ይበለው፤ ከጻድቃኖች ተርታ ያውለው፡ ነፍሥህን ይማር።

ልጅ ነብያት አክሊሉ ደምሴ



NYC, 2016

7 views0 comments
bottom of page