top of page

Remembrance by Menbere Haile, Sisterሐምሌ / July 24/2021


የወንድሜ የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ትንሽ ማስታወሻና የሐዘን እንጉርጉሮ


(የ 40 ቀን መታሰቢያ ሲከበር በታናሽ እህቱ በመንበረ ኃይሌ የተፃፈና የተነበበ)


በመጀመሪያ ሁላችንንም ጠብቆ በሰላም ለዚህ ቀን ያደረሰንን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።


የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች የሆናችሁ እዚህ ያላችሁ ትላልቅ ሰዎች፡ የወንድሜ ወዳጆችና ቤተሰቦች በሙሉ በአንዱና በምወደው ወንድሜ በፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ዕረፍት ምክንያት ብፊታችሁ ሆኜ ሀዘኔን እንድገልጽ ስላደረጋችሁኝ በአክብሮት ምስጋናየን አቀርባለሁ።


የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ያልኩበት ምክንያት አለኝ: ወንድሜ ለሀገሩ የነበረውን ጥሩ ምኞት ሲገልጽ “የተቻለውን ያህል ጥረቱ ይቀጥላል ከዚያም የመከሩ ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ እለምናለሁ” ብሎ በደቂቀ እስጢፋኖስ መቅድሙ ውስጥ በማስቀመጥ በማቴዎስ 9: 37-38 ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል አካፍሎን ነበር።


እና ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ብዙ መከራ በዚህ ሁሉ ሥቃይ እየኖረች ሕዝቧም እንደዚህ መከራውን እያየ ሆኖ ብዙ ምሁር፣ ብዙ አዋቂ፣ ብዙ አገር ወዳዶች አፍርታለች፡ ስለዚህ የወንድሜ ምኞትም ፀሎትም እየተሰማ እንደሆነ አስባለሁ ለማለት ነው፡ በዚህ ሁላችንም ደስ የሚለን ይመስለኛል፡ ለኢትዮጵያ ጠበቆች ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር እውነተኛ አድርጎ እንዲህ እንዲህ

ያሉትን ሰዎች ያብዛልን።


እንግዲህ ወንድሜ ለኔ እግዚአብሔር የሰጠኝ ሰው ነበር። ስለራሴ ልናገር እንጅ ስለሌላው ሁኔታውማ ምን ዓይነት ስው እንደነበር እግዚአብሔር ወዶና ፈቅዶ አገር እንዲያውቀው አድርጎታል፡ በተጨማሪም በጎኑ ላቆመለት መልካም ረዳት ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን: ለኔ ወንድሜ ልዪየ ነበር።


ሰው በልጅነቱ የናቱን ፍቅር የሚያስታውሰውን ያህል እኔ በይበልጥ የወንድሜን ፍቅር አስታውሳለሁ፡ በልጅነቴ ለአንድ ልጅ መደረግ ያለበትን ነገር ሁሉ እያደረገልኝ አደግሁ፡ ለምሳሌ ያህል ከብዙ አንዱን ብናገር ሊያጫውተኝ ታቅፎ ይዞኝ ሲሽከረከር ከላዮ ላይ አልወርድለትም ነበር ከዚያ እንድወርድለት ዘዴ ይፈጥርብኛል፡፡ አብረን ስናድግ ከሱና ካባቴ ጋር በመሆኔ ደስተኛ እንደነበርኩ ይታወስኛል፡ ትንሽ ከፍ እንዳልኩ ብዙ ነገር ሳይገባኝ ተለይቶኝ ወደ ግብፅ ሀገር ሄደ፡ ግብፅ ሲሄድ ቆይቶ ይምጣ ወይም ቶሎ ይመለስ ልጅ ስለሆንኩ አላስበውም ነበር ፡ እንደሚቆይ አለማወቄም በዚያን ጊዜ ረድቶኛል፡ መቆየቱ ቢገባኝ ኖሮ ይጎዳኝ ነበር:: ከዚያም አገሩ ከገባ በኋላ አብረን ሁል ግዜ

1

የምናነሳቸውን የአባታችንንና የአያታችንን (የእናታችንን እናት)ፍቅር እግዚአብሔር ሰጥቶን ኖርን፡ አያታችን ብዙ ስላልቆየችልን ሁላችንም ተሳቀናል። ታላቅ እህታችን ወ/ሮ ጦቢያው ኃይሌ እመሀላችን እንደናትም እንደ እህትም ሆና ስትንከባከበን ኖረናል፡ እህታችን እንደሀገሩ ባሕል እጅግ በጣም ቀጭን ፈታይ ነበረች። ወንድማችን ግብፅ ከሄደ በኋላ በጣም ሙቀት ነው ሲባል ትሰማለች መሰለኝ “እኔን ያንገብግበኝ እኔን ይጥማኝ ውኃ ያ ጌታቸው ኃይሌ ገባ አሉ በረሐ” እያለች እያንጎራጎረች ስትፈትል አጠገቧ ሆኜ አዳምጣት ነበር፡ ታዲያ ይህን ስሰማ ውስጤ በናፍቆት ይጨነቅ እንደነበር እስካሁን አይረሳኝም።


ለትምህርት ውጪ ሀገር በኖረበት ዘመን “እባካችሁ ሐይመትን (ሐይመት ትልቅ እስክሆን ድረስ የምጠራበት የልጅነት ስሜ ነበረ) አስተምሯት ባመት አንድ ልብስና አንድ ጫማ አትንፈጓት” እያለ ይጽፍ እንደነበር አባታችን ይነግረኝ ነበር። ከውጪ ከተመለሰ በኃላ በሥራና በትዳር ላይ ሆኜ ትምህርቴን እንዳሻሽል እርዳታና ግፊት አድርጎልኛል፡ ልጆቼም የተሻለ ትምህርት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሱም አስተዋፅኦ አለበት፡ ለልጆቼም እሱን ማጣት ትልቅ ጉዳት ነው።


ወንድማችን በጨዋታ ጊዜ እንኳን ከአንደበቱ የሚወጣው ቃል ሰውን ያንፃል፡ ወንድማችን ለቤተሰቡ ሁሉ በአድራጎቱም በምክሩም እግዚአብሔር የሰጠን ትልቅ ስጦታ ነበረ።


ሐምሌ / July 24/2021 የወንድሜ የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ትንሽ

ማስታወሻና የሐዘን እንጉርጉሮ


እህቶችህ ሁሉ ወንድም ጥላ የሚሉህ

እኔና ልጆቼ ወንድም ጥላ ያልንህ

እባክህ እንወቅ ዛሬ የት እንዳለህ

ሰዎች ይጠይቁህ ካንተ እንዲገኝ መላ

መናገርህ አይቅር የኔ ወንድም ጥላ


እኔስ ጉዴ ነው ገና ወደፊት

ጉዳይ ሲኖረኝ ልደውልለት

አለመኖሩን ማስብ ስጠላ

አቤት ሳሳዝን ሲቀለኝ ጥላ

ውስጤ ሲታወክ ሲጠፋኝ ዘዴ

ምክሬ ካንተው ይሁን ንገረኝ አንዴ


ለኔ ጉዳይ ሲሉህ ችላ የማትለው

ከምን ጊዜውም ቀን ዛሬ የባሰ ነው

አትጨክንብኝ ሆድ ብሶኛል ምነው

አንዱ የናቴ ልጅ ጣልከኝ እኮ እኔን

አባባ እንዲህ ብሎ ማለት ቀረብን

“አንዳፍታ ላውጋችሁ” ብለህ በነገርከን

ምን ምን እዳሳለፍክ እንዴት እንዳደግን

የምን ቆሎ መቁላት ቂጣ መጋገር

እኔስ ትዝ የሚለኝ ደስታየ ነበር

ካንተና ከአባባ ስውልና ሳድር


አለመመቸቱን ችለህ ውጋቱን

ተቀብለኸው ኖርክ የወንበር ኑሮን

አለን እንድንልህ ለኛ ኖርክልን

እኛም ይሁን አልን መስዋዕትነትክን

ለጠዋት ለማታ ለመስማት ድምፅህን

ወንበር ላይ ቁጭ ብለህ ያን ሁሉ ቁም ነገር

ሰርተኸው አለፍህ ጉድ ነው ያንተ ነገር


በሺ ዘጠኝ መቶ በስልሳ ስምንት

ሞተህ መነሳትክን እኔ አረሳሁት

ተመስገን አምላኬ ስል ነው የኖርኩት

ቤተሰቡ ሁሉ ይሁን ነው ያሉት

ታዲያ አሁን ምን ላርገው ሆዴ

አልችልም አለ ወንድሜን ማጣቴን

አወጀ ዘለለ

እራሴ ታመመ ጨፈረና ሆዴ

ወንድሜን አሰብኩት አልኩኝ የለም

እንዴ? ትልቅ ለውጥ ነው በሕይወቴ

እንግዲህ ይርዳኝ ጌታየ አባቴ

አስቤው ታዝቤው ነበረ ትቼው

የዚህ አለም ነገር እንዲህ አይነት ነው

እርር ድብን ብሎ ደሞ ሳቅ

ወዲያው

አየ ሳቅ አየ ሳቅ እንዲያው መደለል

ተፈጥሮ ሆኖ እንጂ ወደንም አይደል

በሀዘን በጭንቀት ስንብሰለሰል

ይኸን ሁሉ ማለት ይኸን መናገር

ምንም አላፅናናኝ እውነት ብናገር

እተነፍስ ነበር ይቀንስልኝ

ወንድሜን አግኝቼው ትንሽ ቢያዋራኝ

በቃ ልተውህ አላነሳህም

ከፍተህብኛል አንተ አይደለህም

ብወተውትህ መልስ አትሰጠኝም

አልገደደህም እምባየ ሲወርድ

አላየኸኝም ሲጠፋኝ መንገድ

በአባቴም አየሁት በእናቴም አየሁት በልጄም

አየሁት ደሞ አዲስ ሆነብኝ ያሁኑን ፈራሁት

አይዞሽ የሚለኝን ካጠገቤ አጣሁት

እህታችን አልቻለች አልተወያየን

እስቲ እግዚአብሔር ይወቅ እኛ መልስ የለን

ስለተቀበልን ካንተ ብዙ ነገር

ጌታ ይሁን ብለን ፈቃድክን እናክብር

የአባብየ ቅርስ ወንድምየ

ደስ ደስ የሚለኝ አለኸን ብየ

ያላወራነው የተረሳ

አንዳንድ ነገር እንድናነሳ

የማትጨክነው ደጉ ተነሳ

አልወደድንልህም ይኸን ኩርፊያህን

ሽማግሌ እንጥራ የሚያስታርቀን

የደግነትና የቁም ነገር ባሕር

የአባባ ኃይሌ ልጅ የእውቀት ማህደር

አሁንም አስተምር አሁንም ተናገር

እንፈልግሀለን ትጠቅማለህ ላገር

በዚህ ሁሉ ዘመን አብረን ባሳለፍነው

እግዚአብሔር አስችሎህ ለኔ ላደረከው

በመካከላችን ላኖረልን ፍቅር

ምስጋና ይድረሰው፡ ከፍ ይበል እግዚአብሔር

መቼም ያልተለየን የአባታችን አምላክ

የለፋህላትን ኢትዮጵያን ይባርክ

ያሉህን በሙሉ አውቆ የሰጠህን

እግዜር ይባርክልህ ብርቅ ውዶችህን

የኔ ወንድም፡ ያላረክልኝ ነገር የለም

በሕይወቴ ሙሉ አንተ አለህበት

ታናሽ እህትህ መንበረ ኃይሌ


Visiting Wondim Tila and Tye Misrak, NYC, 2018

26 views0 comments

コメント


bottom of page