NYC, Spring 2017
ለፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ
በዋሽንግተን ዲሲ ፣ ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
በ ተ ዘ ጋ ጀ ው የ 40 ቀ ን መ ታ ሰ ቢ ያ ሥ ር ዓ ት ላ ይ
ከክቡር ልጅ መንበረ ያየህይራድ ልጆች የቀረበ።
( አቅራቢ ኢሳይያስ ኃይለማርያም )
JULY 24, 2021 (ሐምሌ 17 ቀን፡ 2013 ዓ ም)
አስቀድሞ፣ በዚህ ስለምንወደው ወንድማችን፣ አባታችን ፣ጋሼ ጌታቸው ኃይሌ የ40 ቀን መታሰቢያ ዝግጅት ላይ ያለንን ስሜት እንድንገልጽ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ዕድሉን ስለሰጣችሁን በጣም እናመሰግናለን።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ወይም እኛ እንደምንጠራው፣ ጋሼ ጌታቸው፤ “አንዳፍታ ላዉጋችሁ” በሚለው የሕይወት ታሪክ መጽሐፉ ዉስጥ “የልጅ መንበረ ዕረፍት የጎዳው ከቤተሰባቸው ቀጥሎ እኔን ነው።” በማለት በአባታችን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ከፍተኛ ኃዘን እንደተሰማው ገልጿል፡፡ እኛም፣ የጋሼ ጌታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በእጅጉ የጎዳንና ያሳዘነን መሆኑን ዛሬ፣ በዚህ ጉባዔ ፊት እንገልጻለን፡፡ የወላጅ አባታችንን ምትክ፤ አጽናኚያችንን፤ መካሪያችንን፤ ሞግዚታችንን ፤
አሳዳጊያችንን፤ ታላቅ ወንድማችንን ፤ አባታችንን ጋሼ ጌታቸዉን ማጣታችን ልባችንን ሰብሮታል ፡፡
በእኛ አባትና በጋሼ ጌታቸው መካከል የስጋ ዝምድና ባይኖርም፣ በሁለቱ መካከል እስከ መጨረሻው የዘለቀ የአባትና የልጅ ያህል ቁርኝት ሊፈጠር የቻለው፣ ሁለቱም የዕውቀትና የአርቆ አስተዋይነት ፀጋን የተላበሱ መሆናቸው ነበረ። አባታችን በግብጽ የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በነበረበት ጊዜ ፣ ጋሼ ጌታቸዉ ካይሮ የኮሌጅ ተማሪ ነበረ፡፡ በዚያን ዘመን በውጭ አገር ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ፣ ጋሼ ጌታችውም ያጋጥሙት የነበሩ አንዳንድ ጉዳዮቹን ለማስፈጸም ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ይመላለስ በነበረባቸው ጊዚያት ከአባታችን ጋር ለመተዋወቅ፣ ለመነጋገርና አሳብ ለመለዋወጥም ቻለ። አባታችንም ጋሼ ጌታቸው ይማርበት ከነበረው ኮሌጅ አስተማሪዎችና እንዲሁም ኃላፊ ወይም ዲን ጋር እየተገናኘ፣ ስለ ጋሼ ጌታቸው የትምህርት ትጋት መከታተል ጀመረ። በዚህም አጋጣሚ፣ ጋሼ ጌታቸው፣ ታታሪ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ አርቆ አሳቢና ለአገሩም አለኝታ ሊሆን የሚችል ወጣት መሆኑን አባታችን ለመገንዘብ ቻለ። ስለሆነም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጋሼ ጌታቸው ኃይሌን ልክ እንደራሱ ልጅ አድርጎ በመቁጠር፣ ከቤተሰባችን ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዲኖረው አደረገ። በካይሮ ግብጽ የተመሠረተው ቤተሰባዊ ቁርኝትም፣ የማይቀረው ሞት ሁለቱንም ተራ በተራ እስከወስዳቸው ጊዜ ድረስ፣ እስከ መጨረሻው ፍቅርን እንደተላበሰ ዘለቀ።፣
“አንዳፍታ ላዉጋችሁ” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ፣ በትምህርቱ እንዲገፋበት ያበረታታው የነበረው፣ ለከፍተኛ ትምህርት እስኮላርሺፕ በማፈላለግ ያማክረውና ይረዳው የነበረው፣ ከጀርመን አገር የዶክትሬት ማዕረጉን አግኝቶ ወደ አገሩ እንደተመለሰም፣ ሥራ መጀመር የሚፈልግበትን መሥሪያ ቤት ሲነግረው፣ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበሩት ለክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ነግሮለት፣ የመጀመሪያ ሥራውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲጀምር ያስደረገው፣ ከወ/ሮ ምሥራቅ አማረ ጋር ተፈቃቅረው ትዳር ለመመሥረት ሲስማሙ ፣ ጋብቻው መሰናክል ሳያጋጥመው እንዲሰምር ፤ ከሙሽሪት ቤተሰቦች ጋር በመገናኘት መንገዱን ያመቻቸለትና ለትዳር ምሥረታ ያበቃው መሆኑንና፣ በጠቅላላ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጥሙት የነበሩትን፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ጉዳዮቹን እንደአባት ሆኖ ያማክረውና ያስፈጽምለት የነበረው የእኛ አባት መሆኑን ዘርዝሯል።
ጋሼ ጌታቸውም ተደርጎልኛል የሚለዉን ውለታ የማይረሳ ቁም ነገረኛ ሰው በመሆኑ፣
• ካይሮ ተማሪ ሆኖ ከተዋወቁበት ጊዜ ጀምሮ፣ አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ፣ በነበረው የሕይወቱ ጉዞ ውስጥ፣ አደረገልኝ የሚላቸውን ውለታዎች፣ “አንዳፍታ ላውጋችሁ” በተባለው መጽሐፉ ዉስጥ አንድ በአንድ ዘርዝሯል፤
• በ2010 ዓ. ም ያሳተመውን፣ “ስለ ግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስታወሻዎች”፣ የተባለውን መጽሐፉን ማስታወሻነት፣ “በትምህርቴ እንድገፋበት ለረዱኝ ለክቡር ልጅ መንበረ ያየህይራድ መታሰቢያ።” በማለት አበርክቷል፤
• ጋሼ ጌታቸው ውለታውን የማይረሳ ለመሆኑ ሌሎችም ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ አንዳንዶቹም ቤተሰባዊ (ወይም private) በመሆናቸውና፣ ከጊዜም አንፃር፣ እነዚህኑ ብቻ በምሳሌነት ጠቅሰን ለማለፍ ተገደናል።
አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ ጊዜ በተወው የጽሑፍ ኑዛዜ፣ የእኛን ትምህርትና አስተዳደግ ፣ የእናታችንን ምቾትና ደህንነት እንዲከታተል፣ በጠቅላላ ቤተሰባችንን፣ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረታችችንና ገንዘባችንን እንዲአስተዳድር ጠቅላላ ኃላፊነት ሰጥቶ ባለአደራና ሞግዚት አድርጎ የሾመልን ጋሼ ጌታቸውን ነበረ። ይህንን ሁሉ ታሪክ ያቀረብነው ጋሼ
ጌታቸው ገና በወጣትነቱና በተማሪነት ዘመኑ ይታይበት የነበረው ታታሪነት፣ አርቆ አስትዋይነት፣ ብልህነትና ጨዋነት፣ በወቅቱ በነበሩ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል ፍቅር፣ ተወዳጅነት፣ አክብሮትና ተአማኒነት አስገኝቶለት እንደነበረ፣ ያመለክታል በማለት ነው።
ጋሼ ጌታቸው ሁልጊዜ ፋታ የማይሰጥ የሥራ ጫና የነበረበት ቢሆንም፣ አባታችን በኑዛዜ የሰጠውን አደራ ሳያጓድልና ሰለቸኝ ፣ ደከመኝ ሳይል በከፍተኛ ጥንቃቄና በፍጹም ታማኝነት ጠብቋል። እኛንም በአገር ውስጥና ወደ አሜሪካም በመላክ እንድንማርና እራሳችንን እንድንችል አድርጎናል። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ለእኛና ለእናታችን ያሳይ የነበረዉ የፍቅርና የአክብሮት ስሜት አባታችን በሕይወት በነበረ ጊዜ ያሳይ ከነበረው የበለጠ እንጂ የቀነሰ አልነበረም። ይህ የጋሼ ጌታቸው ከአባታችን በኑዛዜ የተሰጠዉን አደራ በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት ስሜት የመጠበቅ ስብዕናው፣ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ሳይቀር ተሰምቶ፣ ጃንሆይ ወደ ቤተ መንግሥት አስጠርተውት፣ “ፈቃድህ ቢሆን የልዑል መኮንንን ልጆች አስተዳደግና ትምህርት እንድትከታተልልን እንፈልጋለን” ብለው ጠይቀውት እንደነበረ ፣ “ባንዳፍታ ላውጋችሁ” መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል።
በሞት ከመለየቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፣ ጋሼ ጌታቸው ይታከምበት ወደ ነበረው ኒው ዮርክ ሆስፒታል ልንጠይቀው ሔደን ነበረ። በወቅቱ በሰውነቱ ላይ ተገጥመውለት በነበሩ የሕክምና መሣሪያዎች ምክንያት መናገር ባለመቻሉ፣ ለማለት የሚፈልገውን ነገር የሚገልጸው ተዘጋጅቶለት በነበረው ነጭ ሰሌዳ ላይ በመጻፍ ነበረ። እኛ እፊቱ ቆመን በነበረበት በዚያ ቅጽበት፣ አባታችን በሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት፣ በሞትና በሕይወት መካከል የነበረበት ሁኔታ፣ በጋሼ ጌታቸው ሕሊና ውስጥ መጣበት። ወዲያዉም በዚያን ጊዜ ከአባታችን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተወያየዉን ቁም ነገር፣ እሱ እራሱ በተራው በሞት አፋፍ ላይ እያለ እንደ መሰነባበቻ አደርጎ በጽሑፍ ተረከልን። በዚያች በመጨረሻ የግንኙነታችን ሰዓት ያሳየንም የፍቅርና የአክብሮት ስሜት ሁልጊዜም አብሮን ይኖራል። ከጥቂት ቀናት በኋላ እየደከመው መሔዱን ሰማን፤ ተከታትሎም እስከወዲያኛው ማሸለቡ ተነገረን።
በመጨረሻም ፤ “Behind every Great Man there is a Great Woman.” የሚለዉን አባባል እናስታውሳለን። “ከማንኛዉም ታላቅ ሰው በስተጀርባ፣ ታላቅ ሴት አለች” ለማለት ነው። ከጋሼ ጌታቸው በስተጀርባ፣ ሁልጊዜም፣ ባለቤቱ እህታችን ወ/ሮ ምሥራቅ አማረ አለች። ጋሼ ጌታችውን ታዋቂ እንዲሆን ላደረጉት ስኬታማ ሥራዎቹ ሁሉ፣ የወ/ሮ ምሥራቅ አማረ ድጋፍ አለበት። ጋሼ ጌታቸውም በአንድ ወቅት ስለወ/ሮ ምሥራቅ ሲናገር፣ “ለእኔ ሕይወቴ ነች” ብሏል። ወ/ሮ ምሥራቅ፣ ሐምሌ 5 ቀን 1956 ዓ ም በይርጋ ዓለም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የገባችውን የጋብቻ ቃል ኪዳን በመጠበቅ፣ ልጆቿን በሥርዓት ከማሳደግ በተጨማሪ፣ እስከመጨረሻው ትንፋሹ ድረስ ሳትለየው፣ ባለቤቷን በእንክብካቤ በመያዝ የከፈለችው መስዋዕትነት፣ ያላት ብርታትና ጥንካሬ፣ የሚታይባት የሞራል ልዕልና፣ የምትደነቅ፣ የምትከበር ሚስት፣ እህትና እናት እንድትሰኝ ያደርጋታል። ወ/ሮ ምሥራቅ ፣ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፣ ለአንቺም ለልጆችሽም ረጅም ዕድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር ይስጣችሁ። መጽናናትንም ይስጣችሁ።
የጋሼ ጌታቸውን ነፍስ እግዚአብሔር በአጸደ ገነት፣ ከጻድቃኖች ጎን ያኑርልን፣
እግዚአብሔር ይስጥልን፤ እናመሰግናለን።
With a grandniece
Commenti