አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ
ብፁዑ አባታችን ፣ የሐይማኖት አባቶች ፣ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ቤተሰቦች ፣ ዘመድና ጎደኞች እደምን አደራችሁ !
የፕሮፌሰ ጌታቸውን አርባ እንድንዘክር ፥ አምላካችን በደብረ ሰላም ቅድስት ማሪያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰላም ስላሰባሰበን ክብር ለእርሱ ይሁን ።
የፕሮፌሰር ጌታቸውን ህልፈተ-ሕይወት አስመልክቶ በዘውድ ምክር ቤታችን ስም የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንገልፃለን። የፕሮፌሰር ጌታችውን ነፍሥ እንዲምርልንና ገነት እንዲያኖርልን አምላካችንን እንማፀናለን ፣ እንዲሁም ለመላው ቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን እንመኛለን ። ፕርፌሰር ጌታቸውን የማውቃቸው ለብዙ አመታት ነው ። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚወዱትን ሃይማኖታቸውንና ሃገራቸውን በሚገባ አገልግለዋል ። ሃይማኖታችንን ፣ ባህላችንን እና ታሪካችን እንዳይጠፋ ከብራና የተፃፉ ከአምስት ሺ በላይ ፥ የሃይማኖት መጽሐፍቶች ወደ ዘመናዊ ( ዲጂታል ) በማስደረግ ፣ ጥንታዊ ቅርሶችንም እንዳይጠፉ በክብር እዲቀመጡ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ። የቀድሞ ፋሽስት ኢጣልያን መንግሥት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያኖች ላይ በቀጥታ ባደረሱት ጥፋት እና የጦር ወንጀል ምክንያት ይቅርታ እንዲጠይቁና ለጠፋው የሰው ሕይወት ፣ ለወደመው ንብረት ሁሉ ትክክለኛ ካሳ እንዲከፍሉ ለማድረግ አብረን እንሰራ በነበረበት የአለም አቀፍ ሕብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ብዙ ጥረት አድርገዋል ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ሁል ጊዜ እውቀታቸውን ለማካፈል እና ምክርን ለመለገስ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም ። ፕሮፌሰር ጌታቸውን የሚያህል ታሪክ አዋቂና አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ማጣት ቀላል አይደለም ። ለሃገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ትልቅ እጦት ነው ። የሰው ልጅ የሌላውን ሰው ዘር ፣ ሐይማኖት እና ቋንቋ ለማጥፋት ደባ በሚሰራበት ዘመን ፕሮፌሰር ጌታቸው ከአማርኛ በተጨማሪ የአፍ መፍቻ ልሳናቸው ላልሆኑት ቋንቋዎች እና ባህሎች እውቅና በመስጠት የሌሎቹንም ቋንቋ ፣ ባህል እና ታሪክ ያከብሩ ነበር ። ከማክበርም አልፎ እንደ እብራይስጥ ፣ አረብኛ ፣ ጀርመንኛ ፣ ግሪክ ፣ ላቲን እና ኦሮምኛ የመሳሰሉ ቋንቋዎች ተምረው በመመራመር ምክንያት በዓለም መድረክ አስከብሮቸዋል ፣ አድናቆትንም አትርፎላቸዋል ። ለዚህ ለነበራቸው የላቀ እውቀት ላደረገዋቸውም ጥናታዊ ምርምሮች እና ሞያዊ አስተዋጽኦ የማካርተር ጂኒዬስ ሽልማት የተሸለሙ የመጀመሪያው ትውልደ አፍሪካዊ ናቸው ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው መንፈሳዊና ሳይንሳዊ ትምህርቶችን እስከ ዶክትሬት ድረስ ያገበደዱ እና የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ሥልጣኔ እንድናውቅ እንደ አባ ባህረይ ድርሰቶች እና ባህረ ሃሳብን የመሳሰሉ ብርቅና ድንቅ መጽሐፍቶችን ጽፈዋል ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው አብዛኛውን ሕይወታቸውን በዩኒቨርስቲ ቅጥር ጊቢ ያሳለፉ ቢሆኑም በ1964 ዓ.ም. ለተወሰነ ወራት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማገልገላቸው ሊዘነጋ አይገባም ። ሃገራቸውን እና ሕዝባቸውን በበርካታ መስኮች ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ በፊደል ሰራዊት፣ የመምህራን ማህበር ፕሬዘደንት እስከ ሸዋ ክፍለ ሃገር ሕዝብ ተወካይ በመሆን ሃገር እና ሕዝባቸውን አገልግለዋል ። ለወጣት ተማሪዋችም እንዲሁም ለብዙ የፖለቲካ መሪዎትና ተመራማሪዎችም አስተያየትና ምክሮችን ለግሰዋል ።
ከመቼውም ጊዜ በላይ በሃገራችን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት በሚያስፈልገን ጊዜ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያሉ ሊቅ፣ አዋቂ እና አስታራቂ ሽማግሌዋች ማጣታችን ያሳዝናል ። ስለ እውነተኛው እና ትክክለኛው ማንነታችን እና የታሪካችን ምንጭ ሊያስተምሩን እና ሊያስታርቁን ከሚችሉ ታላቅ ሰዋች አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ነበሩ ። ፕሮፌሰር ጌታቸውን ማጣት የሁላችንም እጦት ነው ። ነፍስ ይማርልን ፣ ለቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ሁሉ በድጋሚ ብርታቱን እና ጽናቱን ይስጣችሁ ።
እግዚአብሔር ሃገራችንን ኢትዮጵያ ይባርክ !
እግዚአብሔር ያክብርልኝ ።
ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕረዝደንት
1
Comentários