top of page

40-Day Remembrance Remarks by Artist Alem Tsehay Wodajo

በሕያውነት መኖር

እንደዚህ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ አይነት አቻ የሌለዉ ምሁር፣ ቃል የሚታጣለት ታላቅ ሰዉ፣ ለመግለጽ የሚከብድ ስብዕና ሲገጥም ከምን ጀምሮ ምን ማለት እንደሚቻል ግር ይላል። ሁላችሁም እንደምታዉቁት፣ ጸሀፊ፣ ደራሲ፣ ተመራማሪ፣ የግዕዝ ስነ ልሳን ሊቅ፣ የብዙ ቋንቋ ባለቤትና የብዙ ብዙ ዕዉቀት ባለቤት ናቸዉ። እንደዚህ እንደሳቸዉ ያለ ሊቅ በዘመናት አንዴ የሚፈጠር እንጂ እንደያዉ ሁልጊዜም የሚገኝ አይደለም። የሀገራችን የኢትዮጵያ አንዱ ትልቅ ስጦታ ከመሆናቸዉ ባሻገር ለዓለም ታሪክ፣ ቋንቋና ዕዉቀት ፈላጊና ተመራማሪዎች ገና ወደፊት መርምሮ ትተዉ ያለፉት ሥራ ለትዉልድ የሚያገለግል ዘመን ተሻጋሪ ነዉ። እንደዚህ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ያለ ቋሚ መዝገብ፣ የዘልዓለም የዕዉቀት ምንጭ ፋይል አስቀምጦ ያለፈ ሰዉ እንደማንኛችንም ሰዉ ነዉ አለፈ ብለን ብናወራም እሳቸዉ ግን የማያልፍ ሥራ ትተዋልና ሁሌም ስራዎቻቸዉ በሰዉ ልጆች እጅ ላይ፣ ድምጻቸዉ በተማሪዎቻቸዉ ጆሮ፣ ዉጤታቸዉ በዓለም ክንዉን ላይ ይኖራል። እኛ እንደከያኒ ባለሙያዎች ከሥራቸዉ ቁጭ ብለን ማዳመጥ የማንሰለች ሥራቸዉን እያገላበጥን መጥቀስ የማናበቃ አንጋጠን ወደላይ በአክብሮት የምንመለከታቸዉ የሥነ ጽሁፍና የኪነ ጥብ ልጆቻቸዉ እጦታችን የሚገለጽበት ቃላት አይኖርም። የምንፈልገዉን ጥያቄ በተመቸን ሰዓት ስናቀርብላቸዉ ደከመኝን ሰለቸኝን የማያዉቁ ሁሌም በትህትና በእርጋታ ከማስረዳት ከማስተማር የማይርቁ ታላቅ ጥላ አባት ነዉ ያጣነዉ። በየመድረኩ ደጋግሜ እንደገለጽኩት እንዲህ እንደሳቸዉ ያለ የሚያበረታ የሚያጎለብት የሚያስተምር ፋና ወጊ የሆነ ብርሃን ማጣት የተወሰኑ ቀናት ሃዘን ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜያችን ሰቀቀን ነዉ።

ለኔ በግሌ ገና በለጋ ዕድሜዬ ብዕር ጨብጬ ፅፌ ለውድድር መድረክ ላይ ስወጣ አቅሜን ያረጋገጡልኝ፣ ተስፋዬን ያበረቱልኝ፣ ከዳኝነት ወንበር ላይ ሆነው አሽናፊነቴን ያረጋገጡልኝ፣ እኚህ ታላቅ ሰው ነበሩ። በዚያም ሳያበቃ የፃፍኳቸውን ፅሁፎች በማንበብ - "ይህን ለምን አልሽ?" "ይህ ምንድን ነው?" እያሉ ከጠባብ ጊዜያቸው ላይ ጊዜ በመስጠት ከአርቆ አሳቢነታቸው እንድማር ከቋንቋ ፋይላቸው እንድቀስም ያደረጉ ታላቅ ሰው ናቸው።

እንዲህ እንደሳቸው ያለ አርአያ የሆነ ሰው ሲያልፍ ትህትናውን ትልቅነቱን ለሌላው ክንድ ሆኖ ማንሳቱን ለመማር ለመኮረጅ መሞክርና እራስን ወደ ውስጥ በመጠየቅ "እኔስ ምን ሰርቼ ላልፍ ነው" በሚል የውስጥ ሙግት ጥፋትም ቢሆን የራስን ድርሻ መወጣት ይገባል። ያኔ ነው ሰው እየተካን ሰው እየፈጠርን ማለፍ የምንችለው። ያኔ ነው የሞተን ማክበር፤ ያለፈን ማድነቅ ብቻ ሥይሆን ያለን ማሞገስ አጠገብ ያለውን መደገፍ የምንማረው። ያኔ ነው ለወገንም ኩራት ለአገርም መከታ የምንሆነው። ያኔ ነው የማይቀረውን ሞት አሽንፈን በሕያውነት ለዘልዓለም የምንኖረው።

እንዲህ እንደ ፕ/ሮ ጌታቸው ሃይሌ ዓይነት ዋርካ ሲወድቅ በሥሩ የተጠለሉት ሁሉ እንደሚጎዱ እሙን ቢሆንም የዘሩት የሚያፈራበት ትተው ያለፉት የሚበራይበት ዘመን ግን ሞልቷል። ይልቁስ ከባህሪያቸው በመውረስ ከታታሪነታቸው በመማር መፅሓፍቶቻቸውን ደጋግሜ በማንበብ ጥቂትም ቢሆን ቁም ነገር በመሥራት ምኞታቸውን እንድንፈፅም አደራዬን አጠነክራለሁ።

እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን!!

ኢትዮጵያ በነፃነቷ ለዘልዓለም ትኑር!!

እግዚአብሔር ያክብርልኝ!!

አለም ፀሓይ ወዳጆ


7 views0 comments

Comments


bottom of page