ከቀድሞ የቪኦኤ ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ
ከሁሉ በፊት ፕሮፌሰር ጌታቸውን በውል የሚያውቁ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያለ ታሪካቸውን የሚናገሩ የሥራ ዘመን አገልግሎታቸውን የሚመሰክሩ እያሉ፤ ይህም እንደተከታተላችሁት በሙሉ ተከናውኗል፤እነዚህ ሁሉ እያሉ ወዳጄ አቶ መክብብ አስታጥቄ “እስቲ አንተም ትንሽ ተንፍስ” ብሎ ለዚህ ክብር ሲያጨኝ ደስታ ብቻ አይደለም ክብርም ተሰምቶኛል።
ምንም እንኳ እነዶክተር አክሊሉ፣ ዶክተር አልማዝ (ዛሬ እዚህ ያሉትን ለመጥቀስ ያህል ነው) ወይም እንደ ሌሎቹ በሥራ ባልደረብነት ባይሆንም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ እርሳቸው መምህር ከነበሩበት ጀምሮ አውቃቸዋለሁ። ያኔ በ1960ዎቹ ቁመተ ሎጋውን፣ መልከ መልካሙን መምህር የማውቀው በርቀት ነበር። ወወክማ (ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) በየሳምንቱ ያዘጋጅ በነበረው ውይይት ከጋዜጠኞች እነአሳምነው ገብረ ወልድ፣ እነሰሎሞን በቀለ፣ እነልዑልሰገድ ኩምሳ፣ እነማዕረጉ በዛብህ፣ እነበዓሉ ግርማ፣ ከሌሎች ምሁራን እነፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ እነፕሮፌሰር ንጉሤ አየለ፣ እነፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ እነፕሮፌሰር ነቢያት ተፈሪ፣ እነፕሮፌሰር አምሳሉ አክሊሉ፣ እነፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለሥላሴ፣ እየተጋበዙ በሚናገሩበት ጊዜ በርቀት በአድማጭነትና በአድናቂነት ነበር ዕውቀቴ። ኮሌጅ በምማርበት ዘመንም የኔን ትልልቆች (ሲንየሮቼን) ሲያስተምር እንጂ እኔ ክፍል ገብቶ አላስተማረኝም። ብቻ ያ መምህር ይደነቅ፣ ይወደድ፣ ብዙ ይወራለት ስለነበር “ምነው አንድ ቀን አንድ ኮርስ እንኳ አስተምሮኝ፣ ፊት ለፊት አናግሬው ጠይቄው” በሚል ጉጉት ነበር የተማሪነት ዘመኔ ያለፈው። ዕውቀቴም በዚህ ደረጃ ነበር። የፕሮፌሰር ጌታቸው ተማሪ የሆንኩት ካረጀሁና፣ ካፈጀሁ ወደዚህ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመጣሁና የቀድሞ መሥሪያ ቤቴን ቪኦኤን ከተቀላቀልኩ በኋላ ነው። ትምርና አያልቅም ሆኖ፣ ትምህርትና ዳገት እያረፉ ነው ሆነና በጋዜጠኝነት ሕይወቴ በሙሉ የፕሮፌሰር ጌታቸው ተማሪ ሆኜ ስኖር ያስጀመሩኝን ትምህርት ሳያስጨርሱኝ፣ ሳያስመርቁኝ እኔ ሳይደክመኝ እርሳቸው ደከሙና አበቁ፣ ዕረፍት አደረጉ።ይቆየን አሉ።
ለማንኛውም የቪኦኤ ጋዜጠኝነት ሞያዬ ምስጋና ይግባውና እጅግ ብዙ ቃለ ምልልሶችን፣ ውይይቶችን ለነዚህ ዝግጀቶቼ ለመሰናዳት ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን የስልክ ጭውውቶችን ሁሉ አድርገናል። እዚህ ዋሺንግተን ዲሲና በሌሎች ስቴቶችም በአካል ተገናኝተን የተወያየንባቸው ጊዜያት አሉ። በወጣትነቴ በተማሪነቴ ያጣሁትን የያን ጊዜውን የቀረቤታ ሁኔታ በስደቱ ዓለም ተወጣሁት። ታዲያ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጣም፣ እጅግ በጣም በርካታ በሆኑ ጉዳዮች ዙርያ መንፈሳዊ በሉት ዓለማዊ፣ ፖለቲካዊ በሉት ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን አስተምረዋል። ኢትዮጵያዊነትን ሰብከዋል። ስለሀገር ፍቅር መሠረታዊ ግንዛቤ አስጨብጠዋል። ሰንደቅ ዓላማ ምንድን ነው? የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ዓርማ እንዴት ይተረጎማል? ሃይማኖትና ፖለቲካ ምንና ምን ናቸው? ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲፋቅ የተጀመረው ዘመቻ እንደምን ይታያል ወይም እንደምን ይገታል? ግዕዝ ለአማርኛ ዕድገት ያደረገው አስተዋጽኦ የመሳሰሉት። በፖለቲካው ዘርፍም የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በየወቅቱ ማስረዳት፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲህ እንደ አሁኑ መላቅጡ ሲጠፋና መያዣ መጨበጫ ሲያጣ የሚሰጡት ጠቃሚ አስተያየት፣ ስንቱ ይቆጠራል? ከዚህ ጋር የተያያዘ አንድ ነጥብ ልጨምር። የኅሊና እስረኛውና ጋዜጠኛው እስክንድር ነጋ የአዲስ አበባ የባልደራስን መልእክት ይዞ ወዲህ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመጣበት ወቅት የአንድ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድንን አሸባሪነት ለማስረዳት ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተጓዘበት ጊዜ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ኒው ዮርክ ድረስ በመሄድ ከጎኑ ከቆሙ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነበሩ።
እኔ ከፕሮፌሰር የተማርኩት ልማርም የምችለው እጅግ ብዙ ነበር። እንደ ብዙዎቻችን እኔም አስተማሪዬን፣ አቅጣጫ ሰጪዬን፣ አማካሪዬን አጥቻለሁ። ይህም በሥራዬ በጋዜጠኝነት ሙያዬ ላይ ከፍተኛ ጉድለት ወይም ክፍተት ፈጠሯል። የሆነ ፕሮግራም ለመሥራት ምሁራንን ለማወያት ሳስብ ከማማክራቸው ሰዎች አንዱ ነበሩ። “እገሌን በዚህ ጉዳይ ባቀርበው” ብዬ ሳማክራቸው በቂ መረጃ፣ ያንን ማጠናከሪያ ጽሑፍ ወይም መጽሐፍ ይጠቁሙኛል። ራሳቸውን ከማወያየት ወይም ከመጠየቅ በዘለለ ፕሮግራሜን አብረውኝ ያዘጋጁ ነበር ለማለት ነው ይህን መጥቀሴ። ልክ ታላቁን ጋዜጠኛ፣ የሙያ አባቴንና፣ አስተማሪዬን ሙሉጌታ ሉሌን ይመስሉኛል። እርሱንም ነፍሱን ይማር። ፕሮፌሰር ጌታቸው በግሌ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለመሥሪያ ቤቴ ለቪኦኤ ትልቅ ውለታ ውለዋል። ወያኔ አዲስ አበባ እንደተቆጣጠረ ቪኦኤ እንዲዘጋ ዘመቻ ሲካሄድ እርሳቸው ለሌሎች ኢትዮጵያውን ምሁራን ጋር ሆነው ፔቲሽን ወይም የመማለጃ ጽሑፍ በማዘጋጀት ታዋቂ የዩናይትድ ስቴት ባለሥልጣናትን በማነጋገር ታድገውታል።
ኢትዮጵያን የሚያፈርስ አንዳች ኃይል ወይም እንቅስቃሴ ሲነሳ አስቀድመው “ኢትዮጵያን አድን” ዘመቻ የሚጀምሩት እርሳቸው ነበሩ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ምንም ዓይነት ክርክርና ውይይት የማይፈሩ፣ ያመኑበትን ነገር ለመናገር ወደ ኋላ የማይሉ፣ የሚቃወሟቸውን ሰዎች እንኳ ፊት ለፊት ግን ደግሞ በሰለጠነ መንገድ የሚሞግቱ፣ የሚከራከሩ ሰው ነበሩ። ክፉ ለዋለባቸው እንኳ መልሳቸው በትኅትና የተሞላ ቂም የማያውቅ ነበር። እዚህ ላይ ሁለት ምሳሌዎችን ላምጣ። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቆሎሳ የኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ስላዘጋጁ መጽሐፉን ፕሮፌሰር ጌታቸው አግኝተነው አንብበው ኖሮ አንዳንድ ግድፈት እንዳገኙበት እና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች መኖራቸውን ገልጸው ተችተዋል። ዶክተር ፍቅሬ የመለሱላቸው ግን፣ እርሳቸውን የማይመጥን ትንሽ ትኅትናም የጎደለው ነበር። ፕሮፌሰር ጉታቸው ግን መልስ ሲሰጡ በተለመደው ጨዋነትና ትኅትና ነበር። ይህም ከማንም፣ ከተቃወማቸው ሰው ጋር እንኳ በትክከል እውነቱን ብቻ በመናገር በግለሰብ ሕይወት ላይ የማይገቡ ነበሩ ለማለት ነው።
ሌላው፣ እርሳቸው ከቂም፣ ከበቀል፣ ከክፋት የራቁ ሰው እንደነበሩ ለማስታወስ የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ከተከፈለ ዘመን ጀምሮ ስደተኛ ይባል ከነበረው ሲኖዶስ አባላት ጋር አንዳንድ አለመግባባት ነበራቸው። አለመግባባታቸው በእርቅ ተወግዶ ሰላም ወረደ ተባለ፤ ሁላችንም ደስ አለን። ወዲያው ፕሮፌሰር ጌታቸው ሎስ አንጀለስ በሚካሄደው የጥምቀት በዓል (ስደተኛው ሲኖዶስ ወይም አባላት ጥምቀትን እዛ ነበር የሚያከብሩት ኤል ኤ ውስጥ) እና ያኔ እኔም በሆነ አጋጣሚ እዛ ሄጄ ፕሮፌሰርን ከነባለቤታቸው ከወይዘሮ ምሥራቅ ጋር አገኘኋቸው። ከቅዳሴ በኋላ ቅዱስ ቁርባንን ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ (በረከታቸው ይደርብን) ሲቀበሉ አየኋቸው። ይበልጥ ኃይለ ቃል የሚመላለሱት ግን ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጋር ነበርና ወደ እርሳቸው ቀርበው በትኅትና ሥጋ ወደሙ ሲቀበሉ ሳይ በጣም ገረመኝ። እንዲህ ዓይነት ሰው ነበሩ። ከቂም የራቁ፣ ተቃውሞን በአግባቡ የሚመክቱ፣ ወደ ግለሰቡ የግል ሕይወት ውስጥ ሳይገቡ ነጥቡ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ሰው ነበሩ። በዚህ በዚህ ትዝ ይሉኛል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ያረፉ ሰሞን “ዝክረ ጌታቸው ኃይሌ” በሚል አንድ የቴሌቪዥን ውይይት ነበረኝ። እዚያ ላይ ትልልቆቻችንን፣ ታሪክ ነጋሪዎቻችንን፣ የሀገር ምስክሮቻችንን ምልክቶቻችንን እያጣን መሆናችንን ተናግሬ ነበር። እስቲ አስቡት ስንቶችን አጣን? እንደ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ፕሮፌሰር ነቢያት ተፈሪ፣ ጋዜጠኛ ጰውሎስ ኞኞ፣ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ፣ ታሪክ ነጋሪ ተክለጸድቅ መኩሪያ፣ ስንቶቹ። እነዚህን የሚተካ ታሪክ ነጋሪ፣ ለሀገር ተቆርቋሪ፣ ምስክርነት ሰጪ፣ እናገኝ ይሆን? ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ የሀገር አውራዎች ተገቢውን ክብር ሰጥተን ይሆን? እንጃ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩበት ጊዜ (ስለብዞዎች ምስክርነት ይሰጡ ነበር በእኔ ራዲዮ) ሲናገሩ “አንድ ሰው ሞተ” ነበር ያሉት። አዎ ለእኔም ዛሬ ፕሮፌሰር ጌታቸውን ሳስብ አንድ ሰው ሞተ እላለሁ። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ አንድ ቤተ መዘክር ጠፋ እላለሁ። በታመሙ ሰሞን ኒው ዮርክ ሳሉ ደውዬ ሳናግራቸው በቪድዮ ቀርጬ ታሪካቸውን በውል ልመዘግብ አስቤ ኮቪድ መጣና አጨናገፈብኝ። ይን አንድ የሚቆጨኝ ነገር ነው። ሌላው ከፍተኛ የኢትዮጵያ ፍቅር ስለነበራቸው ኢትዮጵያ ሄደው ለሚወዷት ሀገራቸው አፈር ቢበቁ ምኞታቸው እንደነበር ታሪካቸው ሲነገር ሰምቻለሁና ሌላው ቁጭቴ ነው። ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ሰው፣ ሲሞቱ ኢትዮጵያ ምድር፣ ኢትዮጵያ አፈር ላይ ቢያርፉ በሚል። ሦስተኛው ቁጭቴ “ስለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የማዘጋጀው መጽሐፍ አለ ቆይ እልክልሃለሁ” ብለውኝ ነበር። ቁጭቴ መጽሐፉን አለማግኘቴ አይደለም። ካላለቀ ወይም ካልታተመ ሳያጠናቅቁ የመሄዳቸው ነገር ነው የሚቆጨኝ። ምናልባት ቤተ ዘመድ ያጠናቅቀው፣ ይጨርሰው፣ ያሳትመው ይሆናል።
ቅድም “ዝክረ ጌታቸው ኃይሌ” የሚል የቴሌቪዥን ዝግጅት ነበረኝ ብያለሁ። አቶ መክብብ ተናገር ሲለኝ “ያንን ፕሮግራሜ ላይ ያቀረብኩትን ቁጭቴን ነው ልናግር የምችለው” አልኩትና እርሱም “አይ ምናለ ታዲያ ጥሩ ነው” ብሎ ስለፈቀደልኝ እዚች ላይ ያን ያልኩትን በመድገም የዛሬ ጽሑፌን እንድቋጭ ይፈቀድልኝ። ያኔ እንደዚህ ነበር ያልኩት መግቢያዬ ላይ ፕሮግራሙን ስጀምር። ዛሬ ዛሬ አሁን አሁን ትልልቆቻችንን እያጣን ነን። የነበረውን የሚነግሩን፣ ያለፈውን የሚያስረዱን፣ የሚያስታውሱን በምስክርነትና በዋቢነት የምናቆማቸውን እየሸኘን ነው። የአንዱን ጉምቱ የሀገር አድባር ሸኝተን ከኀዘናችን ሳንበረታ ሳንጽናና ሌላው ጥሎን ይሄዳል። እንዲህ እንዲህ እያለ ታሪክ ነጋሪ ያለፈውን መስካሪ ሲጠፋ ሀገር እራሷ ልትጠፋ፣ ልትዘነጋ፣ ልትረሳ ትችላለች። ለምን እነዚህ ከሌሉ የመሬቱ መኖር ብቻ ሀገር አይሆንምና። ሀገርም ሀገር የሚባለው ቦታም የሚቀደሰው በሰው ነው። “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” እንዲል።
የክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ማረፍ የተሰማ ሰሞን ይህ ቀደም ሲል ያሠፈርኩት ሃሳብ በብዙዎች አእምሮ ሲመላለስ ሲወጣ ሲወርድ እንደነበር እገምታለሁ። የትልልቆቻችን ማለፍ ያሳስበናል።ተጠያቂ ሲጣታ ታሪክ ይዛባል። በዚህ አኳያ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ማጣት ምን ማለት ነው? አስቡት። ሀገር ምን ታጣለች? የአማርኛና የግዕዝ ሊቁ፣ የሥነ ጽሑፍ ጠቢቡ፣ ጌታቸው ኃይሌ ሲታጣ ቤተ ክርስቲያን ምን ታጣለች? በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ምን ያጣሉ? በተለይ ደግሞ ቤተሰብ፣ የቅርብ ወዳጅ፣ ዘመድ፣ በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ኅልፈተ ሕይወት ምን ያጣሉ? መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው። እንደምታውቁት እንደምትስማሙበትም የነዚህ ታላላቆች ኀልፈት ከማሳሰብ አልፎ ያስቆጫል። በተለይ ተተኪ አለመኖሩን ስናስታውስ።
ሰኔ 3 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ቤተሰብ ያዘጋጀው የመጀመሪያ ልጃቸው ወይዘሮ ርብቃ የላኩልኝና በጸሎተ ፍትሐቱ ላይ ወይም በመታሰቢያ ጸሎቱ ላይ በተነበበ ታሪካቸው ውስጥ የተካተተው ቃል እንዲህ ይነበባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል” እንዳለው መልካሙ ሰውና ጽኑ ሃይማኖተኛ የሆነው ጌታቸውም በሞት ከመለየቱ ጥቂት ሳምንታት በፊት ከፈጣሪው ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆኑን ተናግሮ ነበር። መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ እምነቴን ጠብቄያለሁ በማለት። አዎ ውድ ባል፣ አባት፣ ወንደም፣ አጎት፣ ጓደኛ ባልደረባ፣ አስተማሪ፣ ወንድም ጥላ፣ የሸንኮራው ጀግና፣ መልካሙን ገድል ተጋድለህ ሩጫህን ጨርሰሃል። ያለ ጥርጥር ከፈጣሪህ የወርቅ አክሊል ይጠብቅሃል።
ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ ውድ ታላቅ ወንድሜ፣ ውድ መምህሬ፣ ውድ ኢትዮጵያዊው በሰላም እረፍ። ክቡር ሞቱ ለሰማዕት!!!!
Comentarios