top of page

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (1923-2013 ዓ.ም)


https://www.press.et/?p=89893

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አገራችን ካሏት የግዕዝ ቋንቋ ሊቃውንትና ምሁራን ዋነኛው ባለውለታ ናቸው። በግዕዝ ቋንቋችን ዙሪያም የበርካታ መጻሕፍት ደራሲ ናቸው። የግዕዝ ቋንቋን በልጅነት ዕድሜያቸው በተለምዶ የቄስ ትምህርት ቤት ከሚባለው በመጀመር እስከ አሁን ድረስ እየተጠቀሙበትና የእዚህን ብርቅ ቋንቋ ታሪክ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉም ናቸው።

ከ1945 እስከ 1951 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ በ1952 ዓ.ም ወደ ግብፅ ሄደው በካይሮ ከተማ ኖረዋል። ከዚያም በ1957 ዓ.ም ካይሮ ከሚገኘው የኮፕቲክ ቲዎሎጂካል ኮሌጅ (Coptic Theologi­cal College) በቢ .ዲ. (B.D) እንዲሁም ከአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ኢን ካይሮ (American University in Cairo) በቢ.ኤ. (B.A.) ዲግሪ ተመርቀዋል። በመቀጠልም ወደ ጀርመን አገር በመሄድ ከኤበርታርድ ካሪስ ዩኒቨርሲቲ (Eberthard-Karis Univer­sity) በ1962 ዓ.ም. በሴሚቲክ ፍልስፍና በፒ. ኤች. ዲ. (PHD) ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለአስር ዓመታት አስተምረዋል።

ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ ከ18 በላይ መጻህፍትን ደርሰዋል። ብዙ መጻሕፍትንና ጽሑፎችንም ተርጕመዋል። እጅግ አድካሚ የሆነውን፣ ነገር ግን የአገር ቅርስን በሥርዓት ለማቆየት የሚያስችለውን የኢትዮጵያን ካታሎግ ማኑስክሪፕት አዘጋጅተው በማይክሮፊልም በማድረግ አዲስ አበባ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ማኑስክሪፕት ቤተ-መጻሕፍት እና ኮሌጅቪል፣ ማይነሶታ ለሚገኘው ለ Hill Monastic Manuscript Li­brary አበርክተዋል።

ከመጀመሪያ ሥራዎቻቸውም በ1965 ዓ.ም. ወደ አማርኛ የተረጐሙት የማርክ ትዌይን (Mark Twain) ኣጫጭር ታሪኮች ኤክስትራክትስ ፍሮም ኣዳምስ ዲያሪ (Extracts from Adam’s Diary) የተባለው ነው። ስለ ታዋቂው የጎንዳጎንዳው አባ እስጢፋኖስ በ2006 እና በ2011 ሁለት ጥራዝ መጻሕፍትን ጽፈዋል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው በትርጕም ሥራዎቻቸው የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች፣ የአማርኛ፣ ግዕዝ፣ አረብኛ፣ ሂብሩ፣ ላቲን፣ ግሪክ፣ ጀርመንና ኮፕቲክ ናቸው። የግዕዝ ቋንቋን በተመለከተ በርካታ ሥራዎችን በመሥራታቸው ብዙ ሽልማቶችንና ዕውቅናን አግኝተዋል። በበርካታ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ንግግሮችን (lectures) ሰጥተዋል። ግዕዝን አስመልክቶ በብዙ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ቃለ ምልልሶችም ተሳትፈዋል።

በግዕዝ ቋንቋ ላይ ለአበረከቱት አስተዋጽዖ የማካርተር ፌሎውስ ፕሮግራም ጂኒየስ አዋርድ እና የኤድዋርድ ኡሌንዶርፍ ሜዳል ከካውንስል ኦፍ ዘ ብሪቲሽ ኣካደሚ (Ma­cArthur Fellows Program “genius” award and the Ed­ward Ullendorff Medal from the Council of the Brit­ish Academy) አግኝተዋል።

የዘመናዊና የጥንት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሁፍ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ ያደረጓቸው ምርምሮችና ያሳተሟቸው ጽሁፎች የኢትዮጵያንና የሩቅ ምሥራቅ የክርስቲያን ኃይማኖት አማኝ ወጎችንና ታሪኮችን በማቆየት ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት ኮሌጅቪል፣ ሚነሶታ በሚገኘው የሴይንት ጆንስ ዩኒቨርሲቲ Regents Professor of Medieval Studies and Cata­loguer of Oriental Manuscripts of the Hill Monas­tic Manuscript Library በመሆን ሠርተዋል። ከ5 ሺ በላይ ማኑስክሪፕቶችን ካታሎግ በማድረግ የግዕዝን ማኑስክሪፕት በማይክሮፊልም በማስረዳት አስር ካታሎጎችን ኣሳትመዋል። ይህም ምኑም ሳይጓደል በኢትዮጵያ ብቻ የተገኘውን የሄኖክ መጽሐፍን Book of Enoch ይጨምራል። በእውነቱ ይህ እጅግ ከባድ ሥራ ነው።

በባህል ታሪክና ሥነጽሑፍ ችሎታቸውና ተመራማሪነታቸው በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ታዋቂነትን ያተረፉ ታላቅ ሰው ነበሩ ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ:: ለብዙ ጊዜ በሕመም ቆይተው በ90 ዓመታቸው እንደጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ሰኔ 10 ቀን 2021 ከዚህ ዓለም ዕረፍታቸው ሆነ::

ብዙዎች «የዕውቀት ሁሉ ማህደር» «ተንቀሳቃሽ ቤተመፃሕፍት» ብለው የሚጠሯቸው እኚህ ታላቅ ሰው ዕልፈት ዕውቀት ተጠቅልሎ ወደመቃብር እንደወረደ የሚቆጠር ነው፤ ይላሉ ኘሮፌሰር አዱኛው ወርቁ የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ተመራማሪ።

«በገና ደርዳሪዎች እንዲህ ትልቅ ሰው ሲሞት

እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር

ፆመ ድጓ ይዞ ገባልህ መምህር ይላሉ::

ብዙ ዕውቀትን ነው ተሸክመው የሄዱት የማይተኩ ሰው ናቸው:: የእሳቸውን ፈለግ መከተል ነው እንጂ እርሳቸው ከሚገባው በላይ ግዴታቸውን ተወጥተው አልፈዋል::»

ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነበሩ:: ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ ያበረከቱት አስተዋፅዎ የጎላ ነው:: ጥንታዊ የኢትዮጵያ መዛግብት ጥናት ላይ እስከዘመናቸው ፍፃሜ ድረስ ገፍተውበት ከፍ ያለ እውቅና አግኝተውበታል::

የታሪክ ምሑሩ ዶክተር አሉላ ዋሴ ከጌታቸው ኃይሌ ጋር ቤተሰባዊ ቅርርብ አላቸው:: ኘሮፌሰር ጌታቸውን «የባህልና የታሪክ ጠንካራ ዋልታ» «አስተዋይ እና ጥልቅ ዕውቀታቸውንም ለሌሎች ማካፈል የቻሉ ነበሩ» ሲሉ ይገልጿቸዋል::

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በቀድሞው ሸዋ ክፍለአገር በሸንኮራ ወረዳ ከአባታቸው ከግራዝማች ኃይሌ ወልደየስና ከእናታቸው ወይዘሮ አሰገደች ወልደ ዮሐንስ እንደጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ታኅሣስ 19 ቀን 1931 ነበር የተወለዱት። ከቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ የመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎች አንዱ ሲሆኑ በግብፅ በጀርመን በእስራኤልና በአሜሪካን አገር የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ከፍተኛ እውቅና ያስገኘላቸው ጥንታዊ የኢትዮጵያ መዛግብት ጥበቃ ይደረግላቸው ዘንድ ማይክሮ ፊልም በሚባለው ቅጂ መጠበቂያ እንዲመዘገብ ያደረጉት ጥረት፤ በሜኒሶታ ቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ በማይክሮ ፊልም ተቀርፀው የሚገኙ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚመለከቱ ጥንታዊ የግዕዝ ሥራዎችን ወደአማርኛ የተረጎሙ። ከእነዚህም መካከል ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ የአባ ባህርይ ድርሰቶች፣ ባሕረ ሃሳብ፣ ስለግዕዝ ሥነፅሑፍ የተዘጋጁ አንዳንድ ማስታወሻዎች እና ሌሎች ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ።

ኘሮፌሰር ጌታቸው በእነዚህ ሥራዎቻቸው በርካታ ሽልማቶችን የተቀበሉ ሲሆን ከአፍሪካ የማርካርተር ሽልማትን ያገኙ ብቸኛው ሰው ነበሩ። ከአሜሪካ መንግሥት በ1987 የተበረከተላቸው የማርካርተር የበሳል አዕምሮና ምጡቅ ተመራማሪ ሽልማት በመስኩ የመጀመሪያው ተሸላሚ አድርጓቸው የ340 ሺህ ዶላር አስገኝቶላቸዋል።

«የማካርተር ፋውንዴሽን ግራንት ያሸነፉት ስለኢትዮጵያ የቆዩ መጽሐፍት ላይ የሚያደርጉት ጥናት እየተረጎሙ በመመዝገብ ከሚያደርጉት ጥናት አንፃር ላደረጉት አስተዋፅኦ የ340 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር ያገኙት። በ1987 ለንደን በሚገኘው የብሪታንያ አካዳሚ አባል እንዲሆኑ ተጋብዘው ሄደው ለአባላት የሚሰጠውን ማዕረግ ፌሎው ኦቭ ዘብሪቲሽ አካዳሚ የሚባለውን አግኝተዋል። አካዳሚው በ83 ዓመት ዕድሜው ውስጥ ከዓለም ሊቃውንት መካከል ዝና ያተረፉትን እየመረጠ ነበረ ለአባልነት ይጋብዝ የነበረው። ከዶክተር ጌታቸው በፊትም ሆነ በኋላ አፍሪካዊ ተጋብዞ አያውቅም። ይኽ ነው አንዱ በውጭ የሚታወቁበት። በ1981 በሱዳን የነበሩና በኋላም አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያውያን ከወቅቱ የአሜሪካ ኘሬዚዳንት ቡሽና ምክትላቸውን አግኝተው በአቤቱታ መልክ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ አባት ናቸው።»

ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አዘውትረው በየመገናኛ ብዙኃኑ እየቀረቡ ምሑራዊ ሐሳቦችን ሳይሰስቱና ሳይሰለቹ በማቅረብ ዕውቀትን ሲዘሩ ኖረዋል።

ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኃይሌንና የሰምና ወርቅ አዘጋጆችን ያገናኘን ከልብ የመነጨ የአገርና የወገን ፍቅር ብቻ ነው። ከዚህም የተነሳ የተቻለንን ያህል በአገራችን ሰዎች መካከል እውቀት የዋዛ ፈዛዛ ቀልድንና ቧልትን ተክቶ እንዲገኝ ለማድረግ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ጥረት አድርገን ብዙ ውጤት አስገኝተናል። ሊቁ እድሜ ልካቸውን ለአገራቸውና ለወገኖቻቸው ያለምንም ክፍያ ወይም ጥቅም አገልግሎት በሰጡበት ጊዜ እርግጥ ነው ሥራቸውን ያጠኑና ጠቀሜታውን ያወቁ ለመልካም ዓላማ የተሰማሩ አንዳንድ ድርጅቶች ለሊቁ ሥራ እውቅናን ለመስጠት የገንዘብ ሽልማት አድርገውላቸዋል። ሆኖም ግን ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኃይሌ የተቀበሉትን ገንዘብም ቢሆን አሁንም ለአገራቸው ምሁራን መጠቀሚያ የሚሆኑ የተለያዩ መጻሕፍትን በማሳተም ተጠቀመውበታል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው በጥናቶቻቸው ለረጅም ጊዜና በብዛት የጻፉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። በአማርኛ ደጋግሜ ለመጻፍ የበቃሁት በአቶ አምሐ አስፋው እርዳታና ግፊት ነው ይላሉ። የሚደሰቱበት ትልቁ ተግባርም ምዕራባውያን ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲያጠኑ የሚጠቀሙት መነጽር ምዕራባዊ እንዳይሆን በጎ ተጽእኖ መፍጠራቸውን ነው። የእርሳቸውን ትሑት አማርኛ ‹‹መፈንቅለ ምዕራብ ወመግረሬ ፀር›› እንለዋለን። ስቴፈን ካፕላን የፕሮፌሰር ጌታቸውን በምዕራባውያን አጥኚዎች መካከል መከሠት (ምጽአተ ጌታቸውን) ‹‹አርዕድ አድለቅልቅ – groundbreaking›› ይሉታል። ምጽአታቸውን መፈንቅል ወይም በቤታችን ቋንቋ መግረሬ ፀር ብንል ሲያንሳባቸው ነው። በትሑት አንደበት ካጫወቱን ማሳያዎችን እንቆነጥራለን።

በአንድ ወቅት መጻህፍቶቻቸው ቀስ በቀስ ወጣቱ እየለመዳቸው እያነበባቸው እንደሆነ ሲሰሙ ‹‹በአማርኛ የምጽፋቸው ተፈላጊነት ማግኘታቸው ደስ ብሎኛል። ግን እኔ ባልጽፋቸውም ሌሎች ይጽፏቸው ነበር።

ለእኔ ትልቅ ደስታ የሰጠኝ በውጪው ዓለም ተመራማሪዎች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠሬ_ነው”። “ሳነብ አገርና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጎዳ ነገር ካገኘሁበት በማስረጃ ማስለወጥ እችላለሁ” የምዕራቡን አጥኚ የሚናዝዙ፣ በምዕራቡ ዓለም የነገረ ኢትዮጵያ ጥናት የነፍስ አባት ነበሩ ስንል አንገታችንን ሰገግ ደረታችንን ነፋ አድርገን ነው።

“አንዱ ማስጠንቀቂያዬ ስለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፉ በካቶሊኮች ዐይን እያዩ እንዳይሆን ነው።›› ይላሉ። አውሮፓዊው ሥዕለ ሕሊና ላይ መፈንቅል አድርገዋል ስንል ገቢሩን ዐይተን ሰምተን ነው፡፡

በአውሮፓውያን የኢትዮጵያ ነገረ ክርስቶስ ጥናት ላይ የተካሄደው መፈንቅል እንዲህ ሆነ! ጸጎች በ1870 ዓ.ም. ቦሩ ላይ ተሳደዱ። ግማሹ በግዞት፣ ግማሹ በቅጣት፣ ግማሹ በስደት ተቀጣ። በስደት የሄዱት ወደ ሚሽነሪዎች ተጠግተው አንድ ከባድ በቀል ፈጸሙ። የጸጎች አስተምህሮ ትክክለኛውና ‹‹ተዋሕዶ›› ሊባል የሚገባው የኢትዮጵያ ነገረ ክርስቶስ መሆኑን ጻፉ፤ ተናገሩ። ታመኑ። በእነ ኢግናዚዮ (ኢኛሲዎ) ጕይዲ ተረካቸው ታመነ። ተጻፈበት። የምዕራቡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው እይታ እንዲህ ተቀረፀ። ቀረጻው እዚያው አልቀረም። እነ ዶክተር አባ አየለ ተክለ ሃይማኖትም ኢትዮጵያ ላይ አንፀባረቁት። ምስጋና ለእነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ይሁንና እዚህ (በሀገር ውስጥ) በስዱዳን ጸጎች የተቃኘው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በጸጋ አስተምህሮ የመመልከት ስሑት እይታ ተቀጨ።

በአውሮፓ ግን እስከ ምጽአተ ጌታቸው ድረስ ይህ ሲሆን አልታየም። ጌች ወደ ምዕራቡ ንፈቀ ክበብ ገቡ። ተገረሙ። መፈንቅሉን ጀመሩት። Material on the Theology of Unctionists, The Faith of Unctionists, Ethiopian Heresies and Theological Controversies, Two Am­haric Versions of One Essay in Defense of the Tawa­hido Faith, … በመሳሰሉ ሥራዎች የኢትዮጵያን ነገረ ክርስቶስ መሠረታውያን በውስጣዊ እይታ አነጠሩ፤ የምዕራቡን ዓለም በክልኤ ባሕርይ ተወዳጅተው በስሕተት የቀረፁትን ጸጎች “Crypto-Catholic” (መፍቀርያነ ካቶሊክ) ሲሉ ሚስማር መቱባቸው። ምቱ ለጊዜው በእነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና በመምህራኖቻቸው እነ አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስና አለቃ ተክለ ጽን ላይ በማረፉ በአገር ልጅነት ስሜት መሰቀቅ ቢኖርም ዒማላው በሐዲስ ጸጎች ታዝሎ ሊመጣ ያለውን ካቶሊካዊ ተረክ ሳይነሳ ባለበት መምታት ነበረ። ጌች ዒላማውን አልሳቱም! ጉዳዩን በኢንሳይክሎፐዲያ ኢትዮፒካ በሰፈሩ አጫጭር የነገረ ክርስቶስ ጽሑፎችም አትሞታል! በዚህ ምክንያት ያልጐመጐሙ እንደ አባ ተስፋእዝጊ ዑቁቢት ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያ/ኤርትራ ካቶሊካውያን አጥኚዎች ቢኖሩም አላገገሙም። የጌታቸውን አሰር የተከተለው የቀሲስ ዶክተር መብራቱ ኪሮስ Mia-ph­ysite Christology ተጨምሮባቸዋል። ዋነኛው መግረሬ ፀር ግን እርሱ ነው – ጌታቸው ኃይሌ!

የቆጋው ኢቀኖናዊ ‹‹ሲመት›› በፕሮፌሰር ጌታቸው ዐይን አስቀድመን ፕሮፌሰር ጌታቸው ስለ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽና ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊት ከሚያሰኟት መሠረታውያን አንዱ ብለው በደቂቀ እስጢፋኖስ ተጨማሪ አዲስ መግቢያ ውስጥ ከጻፉልን እንቀንጭብ፡- ‹‹ ሐዋርያዊት ከሚያሰኟት አንዱ መሠረታዊ ምክንያት መሪዋ (ዋናው ጳጳስ) ክርስቶስ ለሐዋርያት የሰጠው ሥልጣን ሲያያዝ መጥቶ ለእሱ ስለደረሰው ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ይኸንን ባህል ለመጠበቅ ብዙ ፈተና አልፋለች። መንፈሳው ሥልጣን ስለሚወረስ፥ ጳጳስ ሲሞት በሐዋርየዊት_ቤተ_ክርስቲያን_ሥርዓት_የጵጵስና_ሥልጣን_ባለው_የበላይ_ጳጳስ_እንጂ_የጵጵስና_ሥልጣን_የሌላቸው_ካህናት_ተሰብስበው_ሌላ_ጳጳስ_መሾም_አይችሉም። ስለዚህ ጳጳሳችን በሞተ ቁጥር በብዙ ጥረት ያልተቋረጠ_ሥልጣን ካለው ከግብጹ ፓትርያክ እናስሾም ነበረ። … የአምላክ ፈቃድ ሆኖ አሁን ቤተ ክርስቲያናችን ራሷን ችላ የራሷን ፓትርያክ ትሾማለች። ››

እንዳንሳሳት ፕሮፌሰር ጌታቸው የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን የተማሩት ከሊቀ ጳጳስና ከፓትርያክ ነው። በኢትዮጵያ የሐዲስ ኪዳን መምህራቸው ቀድሞ ሊቀ ሊቃውንት ይባሉ የነበሩትና በጳውሎስ መልእክታት ትርጓሜ የገነኑት ብፁዕ አቡነ_ጴጥሮስ ሲሆኑ በግብፅ ደግሞ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህራቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ_ሺኖዳ ነበሩ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤያትና በሌሎችም ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች እየወከሉ በተደጋጋሚ ቀርበዋል። Ethiopian Liturgical Christol­ogy የሚል ጥናትም በጉባኤ አቅርበዋል። ስለ ሃይማኖት ሲጽፉ የተራ ምዕመን ጽሕፈት መስሎን እንዳንሳሳት። ስሕተት ወደሌለበት ዓለም የሄዱትን አባት ነፍስ ይማርልን።

ክብርት ባለቤታቸው ወይዘሮ ምሥራቅ ከፕሮፌሰር ሥራ እና አስተዋጽዖ ተለይተው አይታዩም። ወጣት እያሉ እሳቸው እና ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋራ ያሳተሙት “የአዳምና የሔዋን ታሪክ” መጽሐፍ ተጠቃሽ ነው።

ለአገር፣ ለወገን እንዲሁም ለዓለም ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ያሉ ልጆችን ከወይዘሮ ምሥራቅ ጋራ አፍርተዋል። ትልቋ ልጃቸው ዶክተር ርብቃ ጌታቸው በአገራችን እጅግ ዘመናዊ የሆነ አዳሪ ትምህርት ቤት በራሷ ገንዘብ አስገንብታ ትውልድ እያስተማረች ሲሆን፤ ከአራቱ ልጆች ሁለተኛዋ ፕሮፌሰር ሶስና ጌታቸው ደግሞ በአሜሪካ ታዋቂ ሳይንቲስት ናት፤ በቅርቡ በርካታ ሽልማቶችን አግኝታለች። “መልካም ዘር ከነ አገዳው ቸር፤” ይሏል ይሄ ነው።

የፕሮፌሰር ጌታቸውን ዕውቀት፣ አስተዋጽዖ እና ትጋት እንኳን ሊይዙት ጨርሰው ሊዘረዝሩት ይከብዳል። ምናልባት ከሚቀር በአሥር ነጥብ ልግለጻቸው፦

1. የግዕዝ የብራና መጻሕፍትን ሲያውቋቸው ዘመነኛ ያደርጋቸዋል፤ መጻሕፍቱን ያናግሯቸዋል፤ ትንታኔያቸው ሁሌም ድንቅ እና አዳዲስ ዕውቀት የያዘ ነው። በዓለም አቀፍ ጉባዔያት ላይ ሁሌም ተደማጭና በጉጉት ተጠባቂ ናቸው።

2. የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም ዐቀፍ ጉባዔ (Ethiopian Studies) የተሟላ ቅርጽ እንዲይዝ ካደረጉትና በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ከምዕራባውያኑ ተጽዕኖ እንዲላቀቅ ካስቻሉ ምሁራን አንዱ ናቸው። በየጊዜው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ ከመጀመሪያው እስካለፈው ድረስ በመሳተፍና ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ ፕሮፌሰር ጌታቸው ወደር የላቸውም። በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ መገኘት ባይችሉ እንኳ ተጠይቀው ጽሑፋቸው እንዲታተም ይደረጋል። እሳቸው የሚያደርጉትን ንግግር ለማዳመጥ አዳራሽ ይሞላል፤ ከእሳቸው ጋር ፎቶ ለመነሳት ፈረንጁ ሁሉ ይጋፋል “እንኳንም የእኛ ሆኑ” ያሰኛል።

3. የግዕዝ ብራና መጻሕፍን አንድ ባንድ ዘርዝሮ በማጥናት፣ እና መዘርዝር (ካታሎግ) በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ብቸኛው ሲሆኑ፣ ለዘርፉ የዓለም አቀፍ ጥናት ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ከ5ሺ በላይ የብራና ጽሑፎችን አጥንቶ ካታሎግ በመሥራት በዓለም ውስጥ ብቸኛውና ብዙ መጻሕፍትን ያጠኑ ያደርጋቸዋል።

4. የኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ መካከለኛ ዘመን ሲነሳ ተጠያቂ ናቸው። ምዕራባውያን አንዳንዱን ባለማወቅ፣ አንዳንዱን ደግሞ ሆን ብለው ያበላሿቸውን ጉዳዮች በጽሑፋቸው ሞግተዋል፤ አርመዋል። ስለ አገራቸው ኢትዮጵያ ተናግረው አይጠግቡም። የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥነ መንግሥት፣ ሥልጣኔ፣ አስተዳደር፣ ፖለቲካ በቅጡ እንዲታወቅ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ታግለዋል፤ ጽፈዋል፤ ሞግተዋል።

5. የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተሟላ እንዲሆን ካደረጉት ሊቃውንት መካከል ፕሮፌሰር ጌታቸው ግንባር ቀደም ናቸው። በአጥኚ ክፍተት የነበረውን ጉድለት ሞልተዋል፤ የተረሱ የቤተክርስቲያን ታሪክ አጉልተው አሳይተዋል። ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመን ጀምሮ የቤተ ክህነቱን አስተዳደር በቅርብ የሚያውቁና እንዲስተካከልም በብርቱ ሠርተዋል።

6. የቋንቋ ችሎታቸው እጅግ የሚገርም ነው። ግዕዝ የሙያ/ሥራ/ ቋንቋቸው ሲሆን ጽፈውበታል፣ ተርጉመውበታል፣ አስተምረውበታል። ከሴማውያን ልሳናት ዐረቢ እና ዕብራይስጥ በሚገባ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ የማስተካከያ እርማትም ይሰጡባቸዋል። በጽርዕ (ግሪክኛ) (በተለይ ኮይኔ ግሪክ) ይራቀቁበታል። በዚህም የተነሣ የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰብዐ ሊቃናት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዴት ወደ እኛ ቋንቋ እንደተመለሰ እና በብርቱ ጥንቃቄ እንደተተረጎመ አሳይተዋል። በዚህም ከእንግሊዝኛ እና አማርኛ ትርጉም ይልቅ የግዕዙ እንደሚበልጥ ያሳያሉ። (ለናሙና “ነቅዐ መጻሕፍት” ገጽ 16-17 ይመለከቷል)። የቅብጢ ቋንቋ (Coptic) እና የላቲን ቋንቋ ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉባቸው ቋንቋዎች ውስጥ ናቸው። ከአውሮጳ ቋንቋዎች ጀርመንኛውን ተምረውበት የዱክትርና ምርምራቸውን ጽፈውበታል። የእንግሊዝኛ ቋንቋቸው ፈረንጆችን ያስንቃል።

7. ለአማርኛ ቋንቋ ጥናት በተለይም ለጥንት አማርኛ (Old Am­haric) መሬት የሚነቀንቁ በርካታ መጣጥፎች አሳትመዋል። የእርሳቸውን የአማርኛ ጥናት ለሚያነብ ሰው በቋንቋው ዕድገት ከመደነቅም በላይ ቋንቋው በምን ያለ ሳይንሳዊ ዘዴ መጠናት እንዳለት ይማራል። እኔ እንደማስታውሰው ከመጀመሪያዎቹ ምሁራዊ ጽሑፎቻቸው መካከል በJES ያሳተሙት የጥንት አማርኛ ሲሆን፤ የመጨረሻቸው መጽሐፋቸውም ከዚሁ ጋር በተገናኘው (“Teaching and Tradition of the Ethiopian Orthodox Church in Older Amharic”) በሚል የወጣ ነው።

8. የሕይወታቸውን ግማሽ ከ 45 ዓመት በላይ የደርግ መንግሥት ባደረገባቸው ግፍ ቆሞ መሄድ ተስኗቸው በወንበር ተወስነው ኖረዋል። ይሄ ግን ጥናታቸውን አልገታውም። “እንዲህ ባለ አስቸጋሪ የጤና ሁኔታ ላይ ሆነው ነው ብዙ የሠሩት፤ አይከብድም?” ሲባሉ ፤ “እግዚአብሔር ብራናዎቹን ቁጭ ብለህ አጥናቸው ሲለኝ ነው የወገብ ታማሚ ያደረገኝ”፤ ብለው የጸና እምነታቸውን ተናግረዋል።

9. እስከ አሁን ያሳተሟቸው እጅግ በርካታ ሲሆኑ ፦ -ከ30 በላይ ታላላቅ መጻሕፍትን በአማርኛ እና እንግሊዝኛ አሳትመዋል። – 8 ቅጽ የግዕዝ ብራና መዘርዝሮች (EMML cat. vol.4-11) ጽፈዋል። – ከ250 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች በልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ሕትመቶች ላይ አሳትመዋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ከምሁራዊ አስተዋጽአቸው በተጨማሪ አዲሱ ትውልድ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተል ጥረት ያደርጉ ነበር።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015

11 views0 comments

Comments


bottom of page