June 17, 2021
ለሀገር የተኖረ ህይወት!!
መወለድ ፤ ማደግ ፤ መማር ፤ማግኝት እና ማጣት ሂደት በሆነበት ዓለም ሀገረን ሙጥኝ ብሎ ማለፍ ምን ያህል እንደሚያስቀና የፕሮፌሰር ጌታቸው ህይወት ምስክር ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው ከሊቅነታቸው በላይ የኢትዮጲያ ውድ ልጅ ሲሆኑ በተሰማሩበት መስክ ልቀት ካገኙ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን አንዱ እና ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ በመደባበስ ሀገሪቷን ታሪክ አልባ ለማደረግ የተደረገውን ትግል በብዕራቸው እና በእውቀታቸው አጥብቀው የተዋጉና ታሪክንም ፈልፍሎ በማውጣት ለአዲሱ ትውልድ ተሰፋን የሰነቁ ታላቅ ምሁር ናቸው።
ፕሮፌሰር ከሀገራቸው ሲወጡ ኢትዮጵያን እንዳያጡ ስጋት የነበራቸው ቢሆንም ይህ ስጋታቸው እንዴት እንደተቃለለላቸው “አንዳፈታ ላውጋቸሁ” በሚለው የግል ታሪካቸው ውስጥ “ኢትዮጵያን ማጣቴ እንደፈራሁት አልሆነም ፣ ውሎዬ ቀኑን ሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን አንገቴን ደፋ አድርጌ የደብረ ሊባኖስን ፣ የደብረ ሃይቁን ፤ የላሊበላ ገዳማትን መጽሃፍት ሳነብና ከመነኮሳቱ ጋር ሳወራ መንፈሴ ምንም ሳይቀር ጭልጥ ብሎ እንዳጋጣሚ ሰዎች በእንግሊዝኛ እያወሩ በአጠገቤ ሲያልፉ ስስማ ደግሞ ደብረሊባኖስ ፤ ደብረ ሃይቅ ፤ የላሊበላ ገዳሞች ከመቼ ወዲህ በእንግሊዝኛ የሚወራባቸው ሆኑ እሰከ ማለት እደርሳለሁ” በማለት የአሜሪካ ህይወታቸው በኢትዮጵያ ጥናት ላይ ያተኮረ እንደነበር ነግረውናል። እኝህ ታላቅ ሰው በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ካላት “Dilog” መጽሄት ጀምሮ በኢትዮጵያ ጥናት ላይ ከታተሙት የኢትዮጵያ ጥናታዊ ጽሁፎች በአንድ ወቅት ላይ ታዋቂ የነበረችው “Ethiopian Review” መጽሔትን ጨምሮ ብዕራቸው ያልሰፈረበት ህትመት አልነበረም። በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችም ላይ በመቅርብ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ትኩረትን የሚስብ አሰተያየት በማቅረብ የሚታወቁ ሲሆን በሀገራችን የፖለቲካ ግለት ወቅቶች በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሚሰጡት ምሁራዊ ትንተና ድምጻቸው ተናፋቂ ነበር።
የፕሮፌሰርን የስራ ጥልቀት ለመረዳት ሰፊ ምርምር በማደረግ ያጠናቀሯቸውን “ባህረ ሃሳብ ፤ የአባ ባህርያት ድርሰቶች፤ደቂቀ እስጥፋኖስ መጽሀፍትን ጠንቅቆ በማንበብ ምሁራዊ ብስለታቸውን ፣የሃሳብ ንጥረታቸውን ፤ የቋንቋ ጥራታቸውን መገንዘብ ይቻላል። ሥራቸው ሀገርን ከማዳን እና ታሪክን ከማሰተላለፍ አልፎ በዓለም ታዋቂ ከሚባሉ ተቋሞች ትልቅ ከበሬታን ያስገኘላቸው ሲሆን ለብዙ ጊዜ ካገለገሉበት “Saint Johns” ዩንቨርሰቲ ሬጄንትስ ኧሜረተስ ፕሮፊሰር ፤ የብርቲሽ አካዳሚ አባል ፤ የማካርተር ድርጅት ተሸላሚ ሲያደርጋቸው በተለያዩ ሀገር በቀል ድርጅቶችም የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ፕሮፊሰር ጌታቸው “አንዳፍታ ላውጋችሁ” በሚለው የግል ማስታወሻ መጽሀፋቸው ላይ ከፕሬዘዳንት ቡሽ ጋር ያገናኛቸውን አጋጣሚ ሲያወጉ እንዲህ ይላሉ “አንድ ቀን አንድ ሰው ስልክ ደውሎ በእስራት ሰላሉ ሀገሮች “white house” በየአመቱ የመታሰቢያ ክብር እንደሚደረግ ነግሮኝ እኔንም ኢትዮጵያን ወክዬ እንድገኝ ጋበዘኝ። በዕለቱ የተገኝን ተወካዮች ሀገራችን ነፃ ብትሆን ኖሮ እንደዚህ ያሉ ትላልቅ ሰዎችን ታፈራ ነበር በማለት በምሳሌነት እንድናገለግል ነበር”
ፕሮፊሰር ጌታቸው ከኢትዮጵያ ጋር እንደተቆራኙ ነው ያለፉት፤ ኢትዮጵያ ግን ይህን የመሰሉ ምሁር አቅፋ ደግፋ፣ ልጆቿን በልጆቹዋ አስተምራ አክብራ ለመሽኘት አልታደለችም።
ታላቁ ዚቀኛ ትላንት ከኛ ጋር ነበር፤ ዛሬ የለም። ያንን ግዙፍ ስብዕና ሞት ነጠቀን። ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለእውነት እንደቃተተ፣ እንዳስተማረ፣ እንዳቃሰተ እብስ አለ። ልበ ድፍን መሪዎችን፣ ዋልጌ ፓለቲከኞችን፣ አድርባዮችን ግንባሩን ሳያጥፍ በርቱዕ አንደበቱ የሚሞግት የሀገር መከታ ትልቅ ኢትዮጵያዊ አጣን። ታላቅ ምሁር ከነጥልቅ ዕውቀቱ፣ ከነብሩህ ልቡ ለመጨረሻ አሽለበ። ግና ትዝታውና ሥራው ከእኛ ጋር እየኖረ ግዙፍ የቋንቋ ጥናቱ ከትውልድ ትውልድ እየተዘከረ ሕያው እንደሆነ ይቀጥላል።
እኛ የፍኖተ ጥበብ አባላት ከአኝህ እውቅ አትዮጵያዊ ምሁር ብዙ የተማርን ሲሆን በወደፊቱ ትውልድ እና በታሪክ ሰፊ ቦታ የሚኖራቸው ውድ የኢትዮጵያ ልጅ መሆናቸውን ምስክርነት እየሰጠን ፈጣሪ ነፍሳቸውን በቅዱሳን ሰፍራ እንዲያኖር ለቤተሰቡም መጽናናትን እንዲስጥ እንመኛለን።
የግጥም ቋጠሮ ከፍኖተ ጥበብ አባላት ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፦
ከዳዊት ወርቁ
አንደቀጠለ ህይወት በዜማው ያሬድ
ዘርዐ ያዕቆብ ዛሬም ሰው እንድሚያስደንቅ
በጥራት በእውቀት በሥራው ረቂቅ
እውን አይቅሬ ነው
የጌታቸው ህይሌ በሞቱ መድመቅ
ከወንድወሰን ፀጋ
የሜኔሶታው – ድንቁ ሞረሽ ሎሬት፤
ጌትዬ አንቀላፍቶ – አልልም አለ አቤት፤
ጠቢቡ ምዕራፍን አገባዶ – ለብጦ ብራናውን፤
ከ ሀ እስከ ፐ አካሎ – ለትውልድ አሻራውን፤
የዋልድባን፣ የደቀ እስጢፋኖስ – ዘርፎ ቅኔውን፤
ሥልጣነ ግዕዝ ክህነት – ቅርስ አጋምዶ ጦቢያን፤
አዘነ ሚኔሶታ – እጅግ ጎድሎ ኃይላችን፤
ታሪክ ቅርሳችን ቋንቋችንን – ቋጭቶና ለጉሞ፤
ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ አለፈ – ተልኮውን ፈጽሞ።
ከሙሉጌታ አርአያ
አንተ ሃገረኛ አንተ ዚቀኛ ሰው፣
ዛሬ ምነው ደከምክ በቃኝ አልህ ምነው!
ሕያው ሥራዎችህ ዓለም ያደነቀው፣
ደርዝና ጥልቀቱ መለኪያ የሌለው፣
የማይደበዝዙ የስምህ መጠሪያ ያገር ኩራት ናቸው፤
ሐሰትን ገላጩ ስለቱ አንደበትህ፣
ማስረጃ ድጋፉ ሾተላው ብዕርህ፣
የመምሰል በሽታ ሳይጠናወትህ፣
ማጎብደድን ንቀህ ፍጹም ተጠይፈህ፣
ፍርሃት ርዝራዥ ከውስጥህ መንቅለህ፣
መንፈስህ ጠንካራ ፅናትህም ሳይልም፣
ጥበበ ጥልቁ አንተም በአፀደ ሥጋ ላትኖር፣
ሰው ነህና እስከ ዘለዓለም በምድር፣
አፈር ነህና አይቀር ወደ አፈር፣
እንዲይው ዝም……እንዲያው ዝም።
Comentários