መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት (ምሳሌ 12፡4)
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ግዕዝ የማያውቅ ወይም ግዕዝ ለመማር ጥረት የማያደርግ ሰው፣ ስለግዕዝ ሲያወራ ወይም ጥያቄ ሲጠይቅ መስማት የሚያማቸው ይመስለኛል። እኔ ግን እድለኛ ነኝ፤ ስለግዕዝ፣ ስለአማርኛም ሆነ ስለታሪክ የሚረቡትንም ሆነ የማይረቡትን ጥያቄወቼን ስልክ ደውየ እጠይቃቸው ነበር። እርሳቸውም፣ አንዳንዴ ጥያቄዬ እንዳበሳጫቸው ቢሰማኝም፣ በጥሞና ይመልሱልኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ ይህን ማድረግ አልቻልኩም። ደርግ በፈፀመባቸው ግፍ ምክንያት ያደረባቸው ህመም እየፀና፣ እድሜያቸውም እየገፋ ስለመጣ፣ በስልክ ካነጋገርኳቸው ቆየሁ። በአእምሯቸው ያለውን ገና ተመዝግቦ ያላለቀ እውቀት የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘለአለሙ የሚያጣበት ቀን የቀረበ ይመስላል። “የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመልከው አምላክ ምህረቱን ይላክላቸው” ከማለት በስተቀር ሌላ ምን እላለሁ። ሆኖም፣ ምህረቱ ለሳቸው ብቻ አይደለም፤ እውነተኛ እውቀትን ለሚያከብር ሁሉ እንጂ።
እንዲያም ሆኖ ግን፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያደረጉትን አስተዋፅኦ ብቻቸውን አደረጉት ማለት አንችልም። ይስሃቅ ኒውቶን እንዳለው ሁሉ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው አርቀው ማየት የቻሉት በግዙፍ አባቶቻቸው ትከሻ ላይ በመቆማቸው ነው። ካባቶቻቸው የቀረበ፣ አጠገባቸው የሚኖርና ሌት ተቀን የማይለያቸው ሌላ ትከሻ መኖሩን ግን መርሳት የለብንም። ያ ትከሻ፣ የባለቤታቸው የወይዘሮ ምሥራቅ ትከሻ ነውና ልንረሳው አንችልም።
ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ “በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ፣ አንድ አፍታ ላውጋችሁ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፣ የወይዘሮ ምሥራቅን ስም የማያነሱባቸው፣ በውበታቸው የማይፎክሩባቸውና በአርቆ አሳቢነታቸው የማይኩራሩባቸው ገጾች ብዙ አይደሉም። እውነትም ሊኮሩባቸው ይገባል። ደርግ ሰውነታቸውን ቢያቆስልም፣ አእምሯቸውን መንካት ስላቻለ፣ ብዙ ለትውልድ የሚተርፉ ስራዎችን ሰጥተውናል። በነዚህ ስራዎቻቸው ላይ ሁሉ፣ የወይዘሮ ምሥራቅ አሻራ አለበት። ምሁራዊ ጥናታቸውንም ሆነ ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን ለማዳመጥ የሚፈልገው ሰው እጅግ ብዙ ስለሆነ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ብዙ ይጓዛሉ። ያ ሁሉ አስቸጋሪ ጉዞ ያለ ወይዘሮ ምስራቅ ፍቅርና እርዳታ የሚቻል አልነበረም።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ራሳቸው ሁልጊዜ ሲናገሩ እንደሰማናቸው: “እግዚአብሔር ባለቤቴን ወይዘሮ ምሥራቅን ለሕይወቴ የመረጠልኝ ዕለት እንደባረከኝ እቆጥረዋለሁ” ይሉ ነበር፤ አሁንም ይላሉ።: አምሳያ በሌለው ፍቅር እንደሚኖሩ በቅርብም በሩቅም ለሚያያቸው ግልጽ ነው። ደርግ፣ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመው ሊታረም የማይችል ታላቅ ስህተት ከተገበረበት ቀን ጀምሮ፣ ወይዘሮ ምሥራቅ ከባለቤታቸው ጎን አልተለዩም። የፕሮፌሰር ጌታቸውን ስራ ስናደንቅ፣ የወይዘሮ ምሥራቅንም ውለታ ማስታወስ ይኖርብናል።
ኣምሃ ኣስፋው
ሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓም (4/21/2021 ኣእ)
Comments