ከመጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ዶ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ
(የቴክሳስና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ)
“ነበረ ዲበ ሰረገላ፥ ወያነብብ መጽሐፈ ኢሳይያስ ነቢይ።”
“በሰረገላ ተቀምጦ፥ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ ፰፥፳፰)
እንደሚታወቀው፥ በዘመናችን ለቅድስት አገራችን ኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካበረከቱት፥ በትውልዱ ላይ፥ ትልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ከነበሩት፥ እንዲሁም፥ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ፥ በርካታ ሥራዎችን ሠርተው ካለፉት፥ ብርቅዬና ድንቅዬ፥ አገር በቀል ምሁራን መካከል፥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት፥ አንጋፋውና ስመ ጥሩው ሊቅ፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው። ፕሮፌሰር ጌታቸው፥ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ማንነትን፥ ከኦርቶዶክሳዊ ሕይወትና ከዓለም አቀፋዊ ዕውቀት ጋር፥ አስተባብረው የያዙ፥ ደገኛ ምሁርና ታላቅ ቅርስም ነበሩ። በዚህም ምክንያት፥ እነሆ፥ ዜና ዕረፍታቸው፥ በኢትዮጵያውያንና በዓለም አቀፍ ምሁራን ዘንድ፥ ከፍተኛ ኃዘን ከማሳደሩ ባሻገር፥ መለየታቸው በራሱ፥ የታላቅ ቤተ መጻሕፍት መዘጋት፥ የታላቅ ብራና መታጠፍና የዕውቀት ምንጭ መንጠፍ ሆኖ ታይቶአል።
ክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፥ እነሆ፥ ከግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ፥ በአገራችን ኢትዮጵያ የትምህርት መስክ፥ እጅግ በርካታ ሥራዎችን የሠሩ፥ በሙያቸው አያሌ ምሁራንን ያፈሩ፥ በማስተማርና በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፥ ሙያዊ ብቃታቸውን በውል ያስመሰከሩ፥ እንዲሁም፥ አገራችን ኢትዮጵያንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን፥ በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠሩና ያስከበሩ፥ አንጋፋና ባለውለታ ምሁር ነበሩ። በዚህም ዘርፈ ብዙ ችሎታቸውና ሙያዊ ብቃታቸው፥ ከአዋቂነታቸው ጋር፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ፥ ታዋቂነትን ለማትረፍ ችለዋል። ይልቁንም፥ ከላይ በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት፥ የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መሠረት፥ “በመላው ዓለም፥ የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬ” (አውሳብዮስ ዘቂሣርያ)፥ እንዲሁም፥ “ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ፥ የመጀመሪያው ሐዋርያ” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ ዘዔዶም) የተባለው፥ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፥ እነሆ፥ በሰረገላው ተቀምጦ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን፥ ያነብና ይመረምር፥ ምሥጢራቸውንም ጠንቅቆ፥ ያስተውል ነበር። በአንጻሩ፥ ኢትዮጵያዊው ምሁር፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፥ በቅርብ እንደምናውቃቸው፥ የጃንደረባውን ሰረገላ በሚመስለው፥ ዊልቸራቸው ላይ፥ ከ፵፭ ዓመታት በላይ፥ በትዕግሥት ተቀምጠው፥ በጽኑ ዓላማ ታጥቀው፥ ትውልዱን ያስገረሙና ዓለምን ያስደመሙ፥ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተዋል።
ይልቁንም፥ ሊቀ ምሁራን፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፥ በብሩህ አአምሮአቸው አስበው፥ በሰፊ የልቡናቸው መዝገብ አልበው፥ በርቱዕ አንደበታቸው ተናግረው፥ በተባው ብዕራቸው ጽፈው፥ እጅግ በርካታ፥ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን፥ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃም አበርክተዋል። ይኸውም፥ በአገርና በሕዝብ፥ በሃይማኖትና በታሪክ፥ በፖለቲካና በኢኮኖሚ፥ በባህልና በቋንቋ፥ በቤተሰባዊ ኑሮና በማኅበራዊ ሕይወት፥ እንዲሁም፥ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ፥ የሚያጠነጥኑ ናቸው። ከዚህም ጋር፥ የተለያዩ ትምህርታዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን፥ የተደነቁ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን፥ አያሌ የብራና መጻሕፍት፥ ጥልቅ ገለጻዎችንና ዝርዝር ማብራሪያዎችን፥ በጥራት አዘጋጅተውና በትጋት ሰንደው፥ አስረክበውናል። በዚህ ድካማቸውና ውለታቸው፥ እነሆ፥ ታሪክ ዘወትር ሲያስታውሳቸው፥ ትውልድም በክብር ሲዘክራቸው ይኖራል። እኔም፥ ጥሩ ዕድል ገጥሞኝ፥ አንጋፋው ሊቅ፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፥ ከሠላሳ ዓመታት በላይ በቆዩበትና፥ ሕያው አሻራቸውን ባሳረፉበት፥ በኮሌጅቪል፥ ሜኒሶታ በሚገኘው፥ የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ፥ የአንድ ዓመት ቆይታ አድርጌአለሁ። ይኸውም፥ በወቅቱ ለቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ፥ በነገረ መለኮት ትምህርት፥ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፌን ሳዘጋጅ፥ የፕሮፌሰር ጌታቸው ቢሮ በሚገኝበት፥ በሒል ሚዚየምና ሞናስቲክ ላይብረሪ፥ (HMML) ቢሮአችን፥ ፊት ለፊት ስለነበር፥ ከእርሳቸው ጋር፥ የማይረሱ ጊዜያትን፥ አብሬ ለማሳለፍ፥ ከመታደሌም በላይ፥ እነሆ፥ በሺህዎች የሚቆጠሩ፥ የግእዝ መጻሕፍትን፥ በውል ሰፍረውና ቆጥረው፥ በትጋት አንብበውና አመሳክረው፥ በስፋት አጥንተውና መርምረው፥ በዕውቀት አብራርተውና በምሥጢር ተርጉመው፥ በየዓይነቱ ሰንደውና ጠርዘው፥ በውል ተመልክቼአለሁ። በዚህም ምክንያት፥ ለጽሑፌ መነሻ የመረጥኩት፥ “በሰረገላው ተቀምጦ፥ ያነብ ነበር” የሚለው ቃለ መጽሐፍ፥ የዘመናችን አንባቢና ተርጓሚ፥ አርቃቂና ተጠያቂ የነበሩትን፥ ክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን፥ በጕልሕ ይገልጻቸዋል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም፥ ዛሬ ቆመው የሚራመዱ፥ ብዙ ምሁራን፥ በውል ያላሰቡበትንና ያልሠሩትን፥ እርሳቸው ግን፥ በዊልቸራቸው ላይ ተቀምጠው፥ በብቃት አከናውነውታልና። ስለሆነም፥ የታላቁ መምህራችን፥ የሣህለ ማርያም፥ የመጻሕፍት አንባቢነታቸው፥ የሥነ ጽሐፍ ሀብታቸው፥ የዕውቀት ማኅደርነታቸው፥ የጥናትና ምርምር ፍላጎታቸውና ክሂሎታቸው፥ የምሥጢር መዝገብነታቸው፥ ለአገር፥ ለትውልድና ለታሪክ፥ በቅንነትና በኃላፊነት መንፈስ፥ ጠንክሮ የመሥራት ዓላማቸው፥ ለሙያቸው ያሳዩት ትጋታቸው፥ ለቆሙለት ጽኑዕ ዓላማ፥ ያላቸው ታማኝነታቸው፥ ለቤተሰቦቻቸው የነበራቸው፥ ልባዊ ፍቅርና አክብሮት፥ በእኛ በሁላችንም ይደርብን እላለሁ!
በመጨረሻም፥ ከሊቀ ምሁራን፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፥ ሁለንተናዊ ስኬታማነት በስተጀርባ፥ ለአፍታም ቢሆን፥ የማይዘነጉትና ታላቅ ባለውለታ የሆኑት፥ የኑሮ አጋራቸው፥ ውድ ባለቤታቸው፥ ወ/ሮ ምሥራቅ ኃይሌ ናቸው። በመሆኑም፥ እነሆ፥ ቸሩ አምላክ፥ ድካማቸውን ሁሉ፥ ድካመ ቅዱሳን፥ አድርጐ ይቀበልላቸው። ዓስበ መምህራንንም ያድልልን እላለሁ! እንዲሁም፥ ውድ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውንም፥ ስላደረጉት መልካም ነገር ሁሉ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ ልዑል እግዚአብሔር፥ አብዝቶ ይባርካቸው እላለሁ! አሜን❖
Comments