top of page

የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አጭር የሕይወት ታሪክ

በዛሬው ቀን ልንሸኛቸው የተሰበሰብነው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ግንቦት 24 ቀን 1924 ዓ. ም. (June 1, 1932 A.D.) ሸንኮራ ውስጥ ደጎምሲሳ ከሚባል ቦታ ከአባታቸው ከግራዝማች ኃይሌ ወልደየስና ከእናታቸው ከወይዘሮ አሰገደች ወልደ ዮሐንስ ተወልደው በ . . . ዓመታቸው፥ . . . ቀን፥ . . . ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፥ በ1928 ዓ. ም. ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ስለወረረችና የሸንኮራ ሕዝብ ስለሸፈተ በግጭቱ ምክንያት ሴቶችና ሕፃናት ተሰደዱ። ፈረሰኛ ባንዳዎች አገሩን በተደጋጋሚ አቃጠሉት። በዚያው ዘመን አባታቸው የርሔ በሽታ ስላደረባቸው ቤተ ሰቡ ለስደትና ለጠበል ፍለጋ ወደእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት መጡ። አጋጣሚው የቀንና የሌሊት ሀገራዊ ትምህርታቸውን እዚያ ለመጀመር አስችሏቸው ነበር። ግን ሶስት ልጆች ላሉበት ቤተ ሰባቸው ደጉ ጸባቴ ከሚለግሱት ሌላ ምንም ድጋፍ ስለ ሌለ፥ በችግር ምክንያት እናታቸው ልጆቹን ይዘው ወደ ርስት ሀገራቸው ወደ ሸንኮራ ተመለሱ። በዚያ ጊዜ ሀገሩ ባይረጋጋም፥ ኢጣልያኖች ከሰፈሩበት ተጠግቶ ለመኖር ይቻል ነበር። ሆኖም ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ በማሰብ እናታቸው ከካምፖው አውጥተው ወደቱሉ ፈራ ወስደው እዚያ የቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን ተክለው ለሚያገለግሉት አጎታቸው ለደብተራ በላይነህ ወልደየስ ሰጧቸው። በእዚያ ያሳለፉት ያንድ ዓመት ዘመን የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ትምህርታቸውን በጥብቅ ለመከታተል የቻሉት የፋሺስት ወራሪ ኀይል ከኢትዮጵያ እንደወጣ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከመቃብር ቤት ሆነው ልጆች ያስተምሩ ከነበሩት አባታቸው ጋር በኖሩበት ጊዜ ነው። አባታቸው ግራዝማች ኃይሌ ቅኔ ዐዋቂና መጻሕፍት ተመራማሪ ስለነበሩ፥ የግዕዝ ቋንቋ ፍቅር አሳድረውባቸዋል። የሚያስነብቧቸውንም ሆነ በቃል የሚያስጠኗቸውን የግዕዝ ቃል፥ “ይህ ማለት ምን ማለት ነው?” ብለው ሳይጠይቁና ሳይረዱ አያልፉም ነበር። ለዚህም የጠቀማቸው በአፄ ምኒልክ ዘመን የኢትዮጵያ ሊቃውንት ያሳተሙት የአባታቸው መጽሐፈ ሰዋስው ነበረ። ፕሮፌሰር ጌታቸው የአገራችንን ትምህርት ከአባታቸው ስለተከታተሉበት ዘመን ሲጠይቋቸው በደስታ የሚያስታውሱት አባታቸው ባሕረ ሐሳብ ሲያወጡ የሚተቹትን የቅዱስ ድሜጥሮስን ታሪክና የሒሳቡን የአቈጣጠር ስልት ሲሆን፥ በደስታ የማያስታውሱት ለቃል ጥናት አባታቸው በሌሊት በዘንጋቸው የሚቀሰቅሷቸውንና ከጫወታ ሜዳ የሚጠሯቸውን ነው።

 

በዚያው ዘመን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሲከፈት መጀመሪያ በተመላላሽነት በኋላ በአዳሪነት ተመዝግበው የሚሰጠውን ትምህርት በጥሩ ውጤት ስለፈጸሙ፥ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲከታተሉ በ1943 ዓ. ም. (1951 ዓ. እ.) ከአራት ምሩቆች ወጣቶችና ከሶስት መነኮሳት ጋር ካይሮ ወደሚገኝው የቅብጢ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተላኩ። ካይሮ የተላኩበትን መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ይከታተሉ በነበረበት ጊዜ በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ የማታ (Extension) ፕሮግራም ተመዝግበው ስለነበረ፥ በ1949 ዓ. ም. (በ1957 ዓ. እ.) ከቅብጢ መንፈሳዊ ኮሌጅ ባቸለር ኦፍ ዲቪኒቲ፥ ከአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ባቸለር ኦፍ ሶሺያል ሳይንስስ ዲግሪዎች አግኝተው ከሁለቱም የትምህርት ተቋሞች ተመርቀዋል። ለትምህርት ወደ ካይሮ ከሄዱት መነኮሳት መካከል አንዱ የሐዲስ ኪዳን መምህር የነበሩት ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ (ኋላ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ) ስለነበሩ፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ከእሳቸው ዘንድ ትርጓሜ ሐዲስን ለመማር ዕድል አግኝተዋል።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው የወደፊት ሙያቸውን የወሰነላቸው ካይሮ የቀሰሙት ትምህርታቸው መሆኑን ይናገራሉ። በጻፉት የሕይወት ታሪካቸው ውስጥ እንዳሰፈሩት ይሰጧቸው ከነበሩት ቋንቋዎች ውስጥ በአንድ በኩል ዓረብኛና የዕብራይስጥ ቀደም ብለው ከሚያውቋቸው ከግዕዝና ከአማርኛ ጋር መመሳሰል፥ በሌላ በኩል ቅብጢ፥ ግሪክ፥ ላቲን ከነዚያኛዎቹ ቋንቋዎች ርቀው መሄድ ስላስገረማቸው የሚሰጣቸው ትምህርት ከማርካት ይልቅ የበለጠ ለማወቅ መጠማትን አሳድሮባቸው ነበር። እነዚህ ተመሳሳይ ቋንቋዎች የተመሳሰሉት የሴም ወይም ሴማዊ በመባል ዝምድና ስላላቸው መሆኑን ከመምህራቸው እንደተረዱ ያንን የዕውቀት ጥም ለማርካት ሴማዊ የሚባሉ ቋንቋዎችን ሰዋስዋቸውንና ታሪካቸውን መከታተልን ሙያቸው ለማድረግ ወሰኑ። ወስነው አልቀሩም፤ የካይሮ ትምህርታቸውን ከተጠበቀው ምዕራፍ እንዳደረሱ፥ የፈለጉትን ትምህርት ለማግኘት በቀጥታ ከካይሮ ወደ ጀርመን አገር ሄዱ። ጀርመን አገር ትምህርታቸውን በጎቲንገን ዩኒቨርስቲና በቱቢንገን ዩኒቨርስቲ ሲከታተሉ ቆይተው፥ በ1954 ዓ. ም. (በ1962 ዓ. እ.) የዶክትሬት ዲግሪ በማግኘት ተመርቀዋል።

 

በጀርመን አገር በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች ሲዘጉ፥ የአውሮፓን ታሪካዊ ከተሞች እየተዘዋወሩ በመጎብኘት የታሪክ ዕውቀታቸውን ያዳብሩ ነበር። በዚያው ዘመን የመካከለኛው አውሮፓ ኢትዮጵያውያን ማኅበር ፕሬዚዴንት በመሆንም ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል።

 

ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወዲያው ከጀርመን አገር ተመልሰው በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለጥቂት ወራት ካገለገሉ በኋላ በ1956 ዓ. ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል ተቀጥረው ከኢትዮጵያ እስከ ተሰደዱበት እስከ ኅዳር ወር 1968 ዓ. ም. ድረስ በሚመኙትና በሚወዱት የመምህርነት ሥራ ላይ ተሰማሩ። በዩኒቨርስቲ ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ነው የሚለውን የዩኒቨርስቲውን ሕግ በመጣስ በአገር ቋንቋ በአማርኛ ማስተማር ጀመሩ። ብሔራዊ ባህልን ለተማሪዎቹ ለማስተዋወቅ በትርፍ ጊዜያቸው ለማወቅ ከሚፈልጉ ተማሪዎች ጋር ማታ ማታ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይገናኙ ነበረ። የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ መጽሔት ለማቋቋም ባሰቡ ጊዜና አማካሪያቸው እንዲሆኑ በጠየቋቸው ጊዜ ለመጽሔታቸው “እንዲህ ነው” የሚል ስም ያወጡላቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ናቸው። በመጨረሻም የዩኒሸርስቲ ኢትዮጵያውያን መምህራን ማኅበር ፕሬዚዴንት ሆነው ለጥቂት ዓመታት ጓደኞቻቸውን አገልግለዋል።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከወይዘሮ ምሥራቅ አማረ ጋር ሐምሌ 5 ቀን 1956 ዓ. ም. በይርጋለም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሕግ ተጋብተው አሁን በሥራ ዓለም የተሰማሩ ስማቸውና ሞያቸው ቀጥሎ የተዘረዘረውን ልጆች አፍርተዋል፤

 

ከሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ የተመረቁ ወይዘሮ ርብቃ፤

ከኤም አይ ቲ በመሀንዲስነት የተመረቁ ወይዘሮ ሶስና፤

ከዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በኬሚስትሪ የተመረቁ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ፤

ከዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ የተመረቁ አቶ ዳዊት፤

ከማካለስተር ኮሌጅ በኪነ ጥበብ የተመረቁ ወይዘሮ ማርያም ሥና፤

ከዬል ዩኒቨርስቲ በንግድ ሥራ የተመረቁ አቶ ዮሐንስ።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው አስተማሪ በነበሩበት ዘመን ከዩኒቨርስቲው ውጪ በሙያቸው በጽሕፈትም ሆነ በንግግር የኢትዮጵያን ሕዝብ አገልግለዋል። በዚህም ምክንያት ማንበብና መጻፍ ከሚችለው ሕዝባችን ማህል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን በአካል እንኳን ባይሆን በስማቸው የማያውቃቸው ብዙ አይሆንም፤ በተጨማሪም፡

 

∙ የማስተማሪያ መሣሪያ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የፊደል ሠራዊትን አገልግለዋል፤

∙ የአማርኛ አካዴሚ በተቋቋመ ጊዜ ከመጀመሪያዎቹ አባላት አንዱ ነበሩ፤

∙ የምሥራቅ አፍሪካ የቋንቋ ማኅበር አባል ነበሩ፤

∙ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ማኅበር (World Council of Churches) የማእከላዊው ኮሚቴ አባል ነበሩ፤ 

∙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት ኮሚሽን አባል ነበሩ፤

∙ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ማኅበር የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በመወከል አገልግለዋል፤  

∙ ሹመቱን አልተቀበሉትም እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ የቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅነት ሾመዋቸው ነበር፤

∙ በ1966 ዓ. ም. መንግሥት ደብቆት የነበረውን ታላቁን ድርቅ ከዶክተር አብርሃም ደሞዝና ከዶክተር አሉላ አባተ ጋር ወሎ ድረስ ሄደው አይተው ሁኔታውን በጽሑፍ ለዓለም ያስታወቁ ጊዜ ሪፖርቱን ያረቀቁት ፕሮፌሰር ጌታቸው ነበሩ፤

∙ በደርግ ዘመን የሸዋን ጠቅላይ ግዛት ለመወከል ተመርጠው የሸንጎ አባል ነበሩ፤

 

መስከረም 23 ቀን 1968 ዓ. ም. (10/4/1975) የደርግ ወታደሮች ሊይዟቸው ሲመጡ ፕሮፌሰር ጌታቸው እጃቸውን ላለመስጠት ሲዋጉ ስለቈሰሉ፥ በወሩ ለሕክምና ወደ እንግሊዝ አገር ሄደው ወደሚወዷት ሀገራቸው ሳይመለሱ፥ ከሚወዱትና ከሚያስቡለት ወገናቸው ሳይደባለቁ መቅረታቸው ሲያሳዝናቸው ኖሯል። ያም ካልሆነ የዘለዓለሙን ዕረፍት ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ መመለስ ይፈልጉ እንደሆነ በማሰብ ቤተ ሰባቸው የቦታ ምርጫቸውን ቢጠይቋቸው፥ “ቦታ መምረጥ ቢቻል ኖሮ ለምድራዊ ሕይወት ነው እንጂ ለዘለዓለሙ ኑሮማ ቅዱስ ዳዊት “ለእግዚአብሔር ምድር በምልኣ” (ምድር በሞላዋ የእግዚአብሔር ናት) እንዳለው ነውና ለዚያስ ምርጫው የናንተ ጉዳይ ስለሆነ  እሱን ለእናንተ እተወዋለሁ፤ የሀገሬን አየሯን ለመተንፈስ፥ ልጆቿን ለማስተማር በማልችልበት ሁኔታ ምን ላደርግ ብዬ ወደሀገሬ መልሱኝ ብዬ አስቸግራለሁ?” ስላሉ እነሆ ልጆቻቸው ኢትዮጵያን ሳይሆን በቅርባቸው እንዲሆኑላቸው እነሱ የሚኖሩበትን አገር መርጠውላቸዋል።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸውን የደርግ ጥይት አከርካሪያቸውንና የጅማት ስራቸውን ስለጐዳው ከ1968 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ያለውን ዘመን ያሳለፉት በወምበር ወዲያ ወዲህ እያሉ ነበር። ሆኖም በጥይቱ ጠንቅ ምክንያት ቀን ከሌት ሳያቋርጥ በሚገዘግዛቸው ሕመምና በወምበር ላይ መወሰን ሳይሸነፉ፥ ሳያማርሩ፥ የውስጥ ጭንቃቸውን ለቤተ ሰብ ሳያሳዩ፥ የፈለጉትን ሥራ በፈለጉበት ሰዓት ሲሠሩ ኖረዋል። ሕመም እንደሚሰማቸው የሚታወቀው ድርጅቶችና አሳታሚዎች በስብሰባ ላይ እንዲገኙላቸው፥ ለመጽሔቶችና ለኢንሳይክሎፒዲያ የምርምር ጽሑፍ እንዲያቀርቡላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቋቸው፥ “እነዚህን ሰዎች በገዛ እጄ የተሟላ ጤና ያለኝ እንዲመስላቸው አድርጌ፥ ለማረፍና ሕመሜን ለማዳመጥ ዕድል አልሰጥህ አሉኝ” ሲሉ ብቻ ነበር።

 

እውነትም ለሰውነታቸው ዕረፍት በመንሣት ከመቶ በላይ የሚሆኑ ጥናታዊ ድርሰቶች ጽፈዋል፤ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የጻፏቸው መጣጥፎች ቍጥርም እዚያው ይደርሳል። ጥናታዊ ድርሰቶቻቸው በዓለም-አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አትርፎላቸው፥

 

∙ በአሜሪካ ሀገር የGenius Award የሚባለውን ሊቃውንት ሁሉ የሚጓጉትን Macarther Fellow  ሽልማት በ1988 ዓ. እ. ተሸልመዋል፤

∙ በዚያው ዘመን የብሪቲሽ አካዴሚ አባል (Corresponding Fellow of British Academy) እንዲሆኑ ተመርጠዋል፤ ምርጫው ከሰባ ዓመት ዕድሜ በላይ ባለው አካዴሚ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አባል አድርጓቸዋል፤

∙ ሸላሚው ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነው ስለተባለ አልተቀበሉትም እንጂ፥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ለሽልማት መርጧቸው ነበር፤

∙ የኢትዮጵያውያን ዲያስጶራ ለሰብአዊ መብት ስለመከራከራቸውና የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ በስፋት ስለማስታወቃቸው በ1996 ዓ. እ. የዕውቅና ሽልማት ሸልሟቸዋል፤

∙ በዳላስ (ቴከሳስ) የሚገኘው የደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በ1996 ዓ. እ. ሲመረቅ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍና የኢትዮጵን ኦርቶዶክስ ታሪክ ስለማስታወቃቸው የዕውቅና ሽልማት ሸልሟቸዋል፤

∙ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአቶ አሰፋ ገብረ ማርያም ተሰማ አሳሳቢነት ዋሽንግተን ዲ ሲ በምትገኘው በርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በካህናቷም ሙሉ ተባባሪነት በ2001 ዓ. እ. የአክብሮት ድግስ ደግሰውላቸው፥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉባኤ (ኢሀጉ) የዕውቅና ሽልማት ሸልሟቸዋል፤

∙ በቦልቲሞርና ባካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፥ ስለ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የታሪክና የሃይማኖት ላበረከቱት ወደር የሌለው የምርምር አስተዋጽኦ በ1996 ዓ.ም. የዕውቅና ሽልማት ሸልመዋቸዋል፤

∙ የውጪ ሀገር ሕይወታቸውን በሥራ ያሳለፉበት የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርስቲ (ኮሌጅቪል፥ ሚኒሶታ) ለጥቂቶች ምርጥ መምህራን የሚሰጠውን የRegents Professor ማዕርግ ሰጥቷቸዋል፤

∙ ዋሽንግተን ዲ ሲ በምትገኘው በርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተቋቋመው የቅዱስ ያሬድ ማኅበር ጥቅምት 5 ቀን 1999 ዓ. ም. ባደረገው የቅዱስ ያሬድ በዓል ላይ እንዲገኙና ታሪካዊ ትምህርት እንዲሰጡ ጋብዟቸው ስለነበረ፥ ከትምህርቱ በኋላ “በዘመናችን ከሚገኙት ከኢትዮጵያ ዕንቍ ልጆች አንደኛው ምሁር በመሆን በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ እድገት ላደረጉት ግዙፍ አስተዋፅኦ” የምስክር ወረቀት ሰጥቷቸዋል፤

∙ ከ1993 ዓ. እ. ጀምሮ የAnalecta Bollandiana, (Brussels)  (1993- ) አሳታሚ ቦርድ አባል ነበሩ፤

∙ ከ1986 ዓ. እ. ጀምሮ የሚቺጋን ስቴር ዩኒቨርሲቲ የሚያሳትመው  Northeast African Studies, መጽሔት አሳታሚ ቦርድ አባል ነበሩ፤

∙ ከ2011ዓ. እ. ጀምሮ የRaregna di studi etiopici መጽሔት አሳታሚ ቦርድ አባል ነበሩ፤

∙ በ2013 ዓ. እ. የብሪቲሽ አካዴሚ የኤድዋርድ ኡልንዶርፍን ሜዳል ሸልሟቸዋል፤

∙ በ2008 ዓ. ም. “የዓመቱ በጎ ሰው” ሽልማት አግንተዋል፤

∙ በ2017 ዓ. እ. Festschrift ተጽፎላቸዋል፤

∙ በ2018 ዓ. እ. የጳጉሜ ኢትዮጵያ ተሸላሚ ሆነዋል፤

∙ በ2018 ዓ. እ. የአበበ ቢቂላ የእድሜ ልክ አስተዋፅኦ ሽልማት አግኝተዋል፤

∙ በ2018 ዓ. እ. የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ አባል ሆነዋል፤

∙ ኢትዮጵያ የሚታተመው የኢትዮጵያ ጥናት ምርምር መጽሔት አሳታሚ ቦርድ አባል ነበሩ፤

∙ አሜሪካን አገር ይታተም የነበረው የኢትዮጵያን ሬጅስተር ዋና አሳታሚ ነበሩ።

x

በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ዕረፍት ሐዘንተኛ ከሚሆነው ክፍል የትምህርትና የምርምር ጓደኞቻቸው ናቸው። የውጪ ሀገር ሕይወታቸውን በሥራ ያሳለፉት፥ በማይክሮፊልም ተቀድተው በቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርስቲ ቤተ መጻሕፍት የተከማቹትን በብዙ ሺ የሚቈጠሩ የግዕዝና የአማርኛ የብራናና የወረቀት መጻሕፍትን በመመርመር ስለነበረ፥ አጋጣሚው የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍና ታሪክ በማወቅ ረገድ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ሊቅ አድርጓቸው ነበረ። ለምርምራቸው ዋቢ የሚያደርጓቸው እነዚህን ከእሳቸው በቀር ሌላ ተመራማሪ ያላጠናቸውን ምንጮች ስለሆነ ድርሰቶቻቸው ሁል ጊዜ ለአንባቢዎቻቸው አዲስ ዕውቀት የሚያበረክቱ ነበሩ። የምርምር ጓደኞቻቸው አንዳች ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው፥ “ይን ጥያቄ አንተ ካልመለስከው ሌላ ሰው ሊመልሰው አይችልም” የሚል አነጋገር ይጨምሩበት እንደነበረ ይህችን አጭር ታሪካቸውን ስናዘጋጅ ደርሰንበታል። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በማረፋቸው የተውት ትልቅ ክፍት ቦታ የሚሞላው እስኪያገኝ ድረስ ብዙ ዘመናት ያልፋሉ።

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ይኸንን ሁሉ ለመፈጸም የቻሉት ሕመማቸውን በመታገሥ ሲሆን፥ የትዕግሥታቸው ዋና ምንጭ የባለቤታቸውና የልጆቻቸው ደግነትና ፍቅር፥ የብዙ ወዳጆች ጸሎት እንደሆነ ይናገሩ ነበር። የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሞት ቤተ ሰቦቻቸውን፥ እኅቶቻቸውን፥ ዘመዶቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ቢያሳዝናቸውም፥ ከሕመም ተላቅቀው በአምላካቸው መንግሥት ሰላማዊ ዕረፍት ማግኘታቸውን ሲያዩ ይጽናናሉ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ለወገን የተሰጠ ሕይወት መኖራቸው ከመቃብር በላይ የሚኖር የታሪክ ሰው ስላደረጋቸው፥ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ሞት እንዳለያያቸው አይቈጥሩትም። ትዝታቸው፥ ቀልዳቸው፥ ቁም ነገራቸው፥ ኢትዮጵያውያን ከጨቋኝ ገዢዎች ነፃ እንዲሆኑ በብዕራቸው ያደረጉት ትግላቸው፥ የአማርኛቸው ለዛ ሁሉ አብረውን እንዲኖሩ ያደርጓቸዋል።

 

ጌታቸው፥ በቅዱስ ጳወሎስ ቃል፥ ጦርነትን በመልካም ተዋግተሃል፤ የእሽቅድድም ሩጫህን እስከመጨረሻው ሮጠሃል፤ እምነትክን ጠብቀሃል፤ ከእንግዴህ ወዲህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ጠብቆሃል። ነፍስህን ከቅዱሳኑ ጋር ያሳርፍልን፤ አሜን ወአሜን።

FastFoto_0023_a.jpg

 ጌታቸው ከአባቱ ኢትዮጵያ 1962 ዓ.ም

Story Page_FastFoto_0138_a.jpg

ጌታቸው በካይሮ ፣ በ 1950 ዎቹ መጀመሪያ

story page_20210703_121435.jpg

የጌታቸው መታወቂያ ካርድ በካይሮ በነበረበት ወቅት

Story Page_1960s_in_ethiopia_0006_a.jpg

ጌታቸው በካይሮ ፣ በ 1950 ዎቹ መጀመሪያ

Story Page_IMG_20210822_154401_508.jpg

ጌታቸው ከምረቃቸው በፊት ካይሮ ከሚገኙት ጓደኞቻቸው እና መምህራኖቻቸው ጋር

Story Page_0077_a.jpg

ጌታቸው የጀርመን ቻንስለር ሊጎበኙ ሲመጡ በዩኒቨርሲቲው ከአ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር 1972

Story Page_FastFoto_0130_a.jpg

ጌታቸው ከሴት ልጆቹ ጋር በ 1975 አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ የደርግ ወታደሮች ጥቃት ከመፈጸሙ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ

Story Page_FastFoto_0117_a.jpg

ጌታቸው በስቶክ ማንዴቪል የማገገሚያ ማዕከል ፣ አይልስቤሪ ፣ እንግሊዝ ፣ 1976

story page_FastFoto_0085_a.jpg

ጌታቸው በኋይት ሀውስ ሮዝ የአትክልት ስፍራ ፣ የማካርተር ጄኒየስ ሽልማትን ከተቀበለ በኋላ በፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ቡሽ የተሳካ ስደተኛ በመሆን እውቅና ተሰጥቶታል 1988

Story page_FastFoto_0016_a.jpg

-በቅዱስ ጆን ዩኒቨርሲቲ ፣ ሚኔሶታ ፣ ክረምት 1995

EPSON001.JPG

ጌታቸው እና ምስራቅ ፣ 2004

Story Page_FastFoto_0137_a.jpg

ጌታቸው ከልጆቹ ጋር ፣ ገና 1976

Story Page_FastFoto_0133_a.jpg

-ጌታቸው ከምስራቅና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ፣ የገና 2006 ዓ.ም.

bottom of page